በካርዳችን ነገን ለመበየን ዕለቷን እየተጠባበቅን እንገኛለን

You are currently viewing በካርዳችን ነገን ለመበየን ዕለቷን እየተጠባበቅን እንገኛለን

AMN ግንቦት 11/2018 ዓ.ም

ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በወሰዱት የምርጫ ካርድ ሀገርን ለማሳደግ የተሻለ ሀሳብ አለው ብለው የሚያስቡትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ የምርጫ ቀኗን በጉጉት እየጠበቋት እንደሚገኙ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም መራጮች ድምፅ እንደሚሰጡ ይጠበቃል።

የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባም ከየካቲት 28 እስከ መጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም የተከናወነ ሲሆን ሁለት የበዓል ቀናትን ሳይጨምር እስከ ሚያዚያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም በማራዘም ተካሂዶ ተጠናቋል።

በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ድምፅ መስጫ ካርድ ላልወሰዱ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ በዩኒቨርስቲ ለሚገኙ ተማሪዎችና በካምፕ ለሚገኙ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት በልዩ ሁኔታ እስከ ሚያዝያ 24 ቀን 2018 ዓ.ም በማራዘም አጠናቋል።

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ 47 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች 10 ሺህ 934 ዕጩዎችን በማስመዝገብ በመገናኛ ብዙኅን አማካኝነት የፖሊሲ አማራጭ ሃሳባቸውን ለህዝብ በማስተዋወቅ ላይ ናቸው።

መራጮችም በዲጂታል “ምርጫዬ” መተግበሪያና በየምርጫ ጣቢያዎች በአካል በመገኘት ከ50 ሚሊየን 514 በላይ መራጮች ድምፅ መስጠት የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ መውሰድ ችለዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የመዲናዋ ነዋሪዎችም ይበጀናል የሚሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ዕለቱን በጉጉት እየጠበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ካነጋገርናቸው የመዲናዋ ነዋሪዎች መካከል ወጣት መዲና መሀመድ እንዳለችው፤ምርጫ የሀገርን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ለመወሰን የሚያስችል በመሆኑ፤ ሀገርን ያሳድጋል የምትለውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅታለች።

ሌላው አስተያየት ሰጪ አላዛር በለጠ በበኩሉ፤ በወሰደው የምርጫ ካርድ ለሀገርና ለሕዝብ ይጠቅማል የሚለውን ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀቱን ገልጿል።

ለሀገር ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ይበጃል ለሚለው ፓርቲ ድምፅ ለመስጠት የምርጫ ቀኑን በጉጉት እየተጠባበቀ መሆኑንም ተናግሯል።

ምርጫ ለአንድ ሀገር ዲሞክራሲ መሠረት የሚጥልና የሀገሪቱን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ለመወሰን የሚረዳ በመሆኑ፣ ዕለቱን በጉጉት እየተጠባበቀች መሆኑን የገለጸችው ደግሞ ህይወት ገረመው ናት።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አብዲ መካ በበኩሉ፤ የምርጫ ካርዱን ወስዶ ይበጀኛል ይሆነኛል ሀገርን ያሻግራል የሚለውን ፓርቲ ለመምረጥ በጉጉት በመጠባበቅ ላይ መሆኑን መናገሩን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በተጨማሪም ሁሉም ዜጋ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት በዕለቱ ድምጻቸውን እንዲሰጡ ጥሪ አቅርቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review