AMN- ጥቅምት 16/2019 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄዱ ያሉ የልማት እንቅስቃሴዎች የትናንቱን ትውልድ አበርክቶ ያልዘነጉ፣ የዛሬውን ፍላጎት ታሳቢ ያደረጉ እና ለነገው ትውልድም ብሩህ ተስፋን የሚሰንቁ መሆናቸውን የመዲናዋ ነዋሪዎች ገለጹ።
መዲናዋ አዲስ አበባ የልማት ስራዎችን በጠነከረ እቅድ መምራት፣ በተግባር መግለጽ እና በጥራት አጠናቆ ለፍጻሜ ማብቃት ከተያያዘችበት ጊዜ ጀምሮ መሰረተ ልማቶቿ ፍጥነትን፣ ጥራትን እና ትውልድ ተሻጋሪነትን መለያቸው አድርገዋል።
በተለይም ከቀጨኔ አምባሳደር ኢሬቻ እስከ ባምቢስ የሚዘልቀው የወንዝ ዳርቻ ልማት አዲስ አበባ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነቷን ለማረጋገጥ የሰነቀችውን ህልም በተግባር ያሳየ አብነት ሆኗል።
ይህ የወንዝ ዳርቻ ልማት በጉብዝና ዘመናቸው ሀገራቸውን ላገለገሉ የትናንት አዛውንቶች ልዩ ትኩረት የሰጠ ነው፤ የአፍንጮ በር ነዋሪዎቹ አቶ ያሲን ሽፋን እና አቶ ጀማል መሀመድም ልማቱ ለዛለ ሰውነት እረፍትን፣ ለደከመ አእምሮ ደግሞ እውነተኛ ሃሴትን የሚያስኝ መሆኑን አብራርተዋል።

በሌላ በኩል ልማቱ የወጣቶችን ፍላጎት ማዕከል በማድረግ ከዛሬው ትውልድ ጋር በተሰናሰለ መልኩ የተገነባ ሲሆን፣ የብስክሌት ስፖርተኞቹ ህመድግባድ ድልድዩ ፣ ሲፈን ፈይሳ እና ነቢል አብዱልሰላም በፊልምና በማህበራዊ ትስስር ገጾች ብቻ የምናያቸውን ዘመናዊ ልማቶች በደጃችን ያመጣ ነው ሲሉ ምስክራቸውን ሰጥተዋል።
የልማቱ ሌላኛው ማራኪ ገጽታ የነገ ተስፋ ለሆኑ ህፃናት የደስታና የሃሴት ማዕከል መሆኑ ነው፤ ቀደም ሲል በአፈርና በውሃ መጫወት ለኢትዮጵያዊያን ታዳጊዎች አዳጋች የነበረ ቢሆንም፣ ዛሬ ግን በልማቱ ውስጥ ሰፊ ስፍራ ተሰጥቷቸዋል።
የልጆቻቸውን ደስታ ሲመለከቱ የተሰማቸውን ስሜት ያካፈሉት ወላጆች ወይዘሮ ሱናማዊት ሽመልስ እና አቶ ምትኩ በቀለ እንዲሁም ህፃን ዙለይካ ኸይረዲን እና አሚናዳም ሰለሞን የልማቱ ተጠቃሚ በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
በመጨረሻም የመዲናዋ ነዋሪዎች እነዚህን ዘመናዊና ትውልድ ተሻጋሪ የልማት አውታሮች መጠበቅና መንከባከብ የጠቅላላው ህብረተሰብ ዋነኛ የቤት ሥራ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።
በተመስገን ይመር