የኢትዮጵያ የማይቀረው የባህር በር ባለቤትነት

AMN- ጥቅምት 4/2019 ዓ.ም

በአፍሪካ ቀንድ በቆዳ ስፋቷ፣ በሕዝብ ቁጥሯ እና በኢኮኖሚ እንቅስቃሴዋ ታላቅ የሆነችው ኢትዮጵያ፣ ከቀይ ባህር ጋር ያላት ግንኙነት የቅርብ ጊዜ የፖለቲካ ፍላጎት ሳይሆን በታሪክ፣ በጂኦግራፊ፣ በኢኮኖሚ እና በደህንነት የተሳሰረ የህልውና ጉዳይ ነው።

የቀይ ባህር ቀጣና በዓለም አቀፍ ደረጃ በቀን አስር ከመቶ በላይ የሚሆነው የንግድ ፍሰት እና ከፍተኛ የነዳጅ ምርት የሚያልፍበት ስትራቴጂካዊ መስመር ሲሆን በዚህ ቀጣና ውስጥ ኢትዮጵያ ያላት ታሪካዊ ድርሻ እና ወቅታዊ ፍላጎት የማይቀየር እውነታ ነው።

ታሪካዊ ማስረጃዎች እንደሚያስረዱት፤ በታላቁ የአክሱም ሥልጣኔ ዘመን ኢትዮጵያ በቀይ ባህር በኩል ከአረብ፣ ከህንድ፣ ከሜዲትራኒያን ሀገራት እና ከሮማውያን ግዛት ጋር ሰፊ የባህር ንግድ እና የዲፕሎማሲ ግንኙነት ነበራት።

በዘመኑ የነበረው የታሪካዊው የአዱሊስ ወደብ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ የቀይ ባህር ንግድ የበላይነትና የባህር ኃይል እንደነበራት ህያው ምስክር ነው።

በተጨማሪም እስከ 1985 ዓ.ም ድረስ ኢትዮጵያ ረጅም የቀይ ባህር ጠረፍ እንዲሁም የምጽዋ እና የአሰብ ወደቦች ባለቤት የነበረች ሲሆን የኤርትራ ከኢትዮጵያ መለየትን ተከትሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሕዝብ ቁጥር ግዙፍ የሆነችው ሀገር የባህር በር አልባ ሆናለች።

ይህም በወቅታዊው የኢኮኖሚ እውነታ ሲመዘን፣ የኢትዮጵያ ፈጣን እድገት እና የሕዝብ ቁጥር ብዛቷ የባህር በር ጥያቄዋን ህልውናዊ ያደርገዋል።

አሁን ላይ ከ130 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ የባህር በር አልባ ሀገር እንደሆነች ይነገራል፡፡

የዚህን ያህል ሰፊ ሕዝብ፣ ገቢና ወጪ ንግድ በአንድ ጎረቤት ሀገር ወደብ ብቻ ለማስተናገድ መሞከር በኢኮኖሚክስ ህግ እንደማይቻል ነው የዘርፉ ምሁራን የሚያስረዱት፡፡

በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ ለዓለም አቀፍ ንግዷ ከ90 ከመቶ በላይ በጅቡቲ ወደብ ላይ የምትጠቀም ሲሆን ለዚህ አገልግሎት ብቻ በየዓመቱ ከ1.5 እስከ 2 ቢሊየን ዶላር የሚደርስ የሀገር ሀብት ለወደብ ኪራይ እንደምታወጣ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ይህ ከፍተኛ ወጪ በሀገሪቱ ለሚከናወነው ለትምህርት፣ ለጤና እና ለሌሎች መሠረተ ልማቶች ቢውል ኢትዮጵያ ለሰነቀችው የብልፅግና ጉዞ ምን ያክል አስተዋጽኦ ሊያበረክት እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡በዚህም አስተማማኝ የረጅም ጊዜ የወደብ አማራጭ ማግኘት ወሳኝ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ አሳማኝ ሕጋዊ እና ጂኦፖለቲካዊ መሠረት ያለው መሆኑ በዓለም አቀፍ የባህር ህግ ድንጋጌዎች መሠረት የባህር በር የሌላቸው ሀገራት በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን ስምምነቶች አማካኝነት ወደ ባህር የመድረስ፣ የመሸጋገር እና የባህር ሀብቶችን የመጠቀም ፍትሃዊ መብት ተሰጥቷቸዋል።

ስለዚህ ኢትዮጵያ ይህንን ዓለም አቀፋዊ መብቷን በመጠቀም በሰላማዊ፣ በዲፕሎማሲያዊ እና ፍትሃዊ በሆነ የጋራ ተጠቃሚነት መርህ የባህር በር እንድታገኝ የሚደረገው ጥረት ሕጋዊ መሠረት ያለው ትክክለኛ አካሄድ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሰላም፣ በፍትሃዊ ንግድና በጋራ የልማት ስምምነት የሚፈታ እና ሊታለፍ የማይችል የረጅም ጊዜ የሕልውና እና የብሔራዊ ደህንነት ጥያቄ ነው።

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review