AMN- ጥቅምት 18/2019 ዓ.ም
የመደመር መጽሐፍ ወደ ሩሲያኛ ቋንቋ ተተርጉሞ ለንባብ መብቃቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልእክት፤ በመጽሐፉ የምረቃ መርሃ ግብር ላይ በአካል ተገኝቼ በመካፈሌም ታላቅ ደስታና ኩራት ተሰምቶኛል ብለዋል፡፡
ይህ ታሪካዊ ስኬት የመደመር ፍልስፍና ከኢትዮጵያ አገር በቀል እውቀት ተነስቶ ዛሬ ላይ ድንበር በመሻገር ወደ መላው ዓለም እየሰፋ መሄዱን የሚያሳይ ህያው ማረጋገጫ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በፊት መጽሐፉ ከአገር ውስጥ ቋንቋዎች በተጨማሪ በእንግሊዝኛ፣ በቻይንኛ እና በአረብኛ ቋንቋዎች ተተርጉሞ ለብዙኃን አንባቢያን መድረሱ ይታወሳልም ነው ያሉት፡፡
አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ሀሳብ ድንበር ተሻግሮ በሰፊው የሩሲያኛ ተናጋሪ ደጃፍ መድረሱ የፍልስፍናውን ዓለም አቀፋዊ ተደራሽነትና ዲፕሎማሲያዊ ፋይዳ ይበልጥ ያጎለብተዋል ብለዋል፡፡
ይህ እርምጃ የመደመርን ፍልስፍና፣ እሴቶችና ሀሳቦች ከኢትዮጵያ አልፈው ለሌሎች ሕዝቦች የሚደርሱበትን አዲስ ዕድል ከመፍጠሩም በላይ፣ ኢትዮጵያ ለዓለም የምታበረክተው የራሷ የበሰለ ሀሳብ እንዳላት በተግባር እንደሚያሳይም አንስተዋል፡፡

ሩሲያ ለብዙ ኢትዮጵያውያን የሥነ ጽሑፍና የዕውቀት መማሪያ ምድር ሆና እንዳገለገለች ሁሉ፣ አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ሀሳብ በሩሲያኛ ቋንቋ ለሩሲያ አንባቢያን መድረሱ የዕውቀት ልውውጡን ሙሉ ያደርገዋል ብለዋል።
ለዚህ ስኬት መሳካትና ለመጽሐፉ ዝግጅት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱትን የሩሲያ ቱዴይ (RT) የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እና አመራሮች ያደረጉትን ጥረትና ትጋት በከፍተኛ ደረጃ አደንቃለሁ ሲሉም ገልጸዋል።
ይህ አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ የኢትዮጵያን የበለጸጉ አገር በቀል እውቀቶች፣ ባህሎችና ፍልስፍናዎች በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ይበልጥ ለማስተዋወቅና በሕዝቦች መካከል ጠንካራ የባህልና የሃሳብ ድልድይ ለመገንባት የሚኖረው ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡