AMN መስከረም 4/2019
18ኛው የብሪክስ ጉባኤ የጥምረቱ አባል ሀገራት መሪዎች በተገኙበት “ጽናትን፣ ፈጠራን፣ ትብብርንና ዘላቂነትን መገንባት” በሚል መሪ ሀሳብ በህንድ ኒውዴልሂ ተካሂዷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የልዑክ ቡድናቸው በዚሁ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ በሚፈጥረው ጉባኤ ላይ የተሳተፉ ሲሆን የጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የልዑክ ቡድናቸው የብሪክስ ጉባኤ ተሳትፎ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ነበረዉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚህ ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር የብሪክስ ጉባዔ የጋራ ትብብርን ወደ የጋራ እሴት፣ ጽናት እና ዘላቂ ዕድገት የመለወጥ ሰፊ አቅምና ቁርጠኝነት እንዳለዉ አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል፤ በጤና ቅድመ መከላከል፤ በህክምና ቁሳቁሶችና መድኃኒቶች ማምረት፤ በዲጂታል ስርዓት ሽግግርና ደኅንነቱ የተጠበቀ አጠቃቀም፣ በመደመር ሰው ሰራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ ግንባታ እና በመሰል የልማት ትብብሮች ከጥምረቱ አባል ሀገራት ጋር አብራ ለመስራት ተነሳሽነት እንዳላት ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአውሮፓውያኑ 2027 COP 32 ጉባኤን በአዲስ አበባ ለማስተናገድ የተጣለባትን ኃላፊነት በተግባርና በተስፋ እንደምትወጣው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እስከ COP 32 ድረስ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ወደ ስምምነት የሚቀይር “የብሪክስ አስተባባሪ መስመር” እንዲቋቋምም ሃሳብ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ ለዚህ አጋርነት የበኩሏን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ መሆኗን ነዉ ጨምረዉ የተናገሩት፡፡
ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት፤ በዲጂታል ስርዓት ማሻሻያ እና ትግበራ እንዲሁም በታዳሽ ሀይል ማስፋፋት እና በኢንዱስትሪ መሠረት ልማቶች አመርቂ ዉጤቶችን በማስመዝገብ ላይ ትገኛለች፡፡
በግብርና ስርዓት ማሻሻያ እየተመዘገቡ ያሉ የምግብ ሉዓላዊነት መረጋገጥ ብሎም ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ግዙፍ የአየር መንገድ ግንባታ በጥምረቱ ለሚነሱ ተያያዥ የውይይት አጀንዳዎች መሪ ተዋናይ እንድትሆን አስችሏታል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከመሪዎቹ ጉባኤ ጎን ለጎን ከአባል ሀገራቱና አጋር ሀገራት መሪዎች ጋር በሁለትዮሽ የሀገራቱ ትብብር ዙሪያ ፍሬያማ ውይይቶችንም አካሄደዋል፡፡
በኢንቨስትመንት፣ ቀጣናዊ ጉዳዩች፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የአቅም ግንባታና ክህሎት፣ ቱሪዝም፣ የማዕድን ልማት እና ወደ ኮፕ 32 በሚደረገው ጉዞ ላይ ሊኖሩ ስለሚችሉ ትብብሮችም በጥልቀት ተወያይተዋል።
በወንድማገኝ አሰፋ