AMN – ጥቅምት 19/2019 ዓ.ም
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ የሀገሪቱን አንድነትና ነጻነት ከውጭና ከውስጥ ከሚሰነዘሩ አደጋዎች በመከላከል የሰማይን ሉዓላዊነት በማስጠበቅ ላይ ይገኛል።
አየር ኃይሉ የኢትዮጵያን አየር ክልል በንቃት ከመጠበቅ ባለፈ፣ በሀገር ውስጥ የሚከሰቱ ሉዓላዊነትን የሚፈታተኑ ስጋቶችን በመመከት የሰራዊቱ ጋሻና መከታ ሆኖ እያገለገለ ነው።
ተቋሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እየተጠናከረ በማንኛውም ሰዓትና ሁኔታ ፈጣን ምላሽ በመስጠት የብሔራዊ ደህንነት ዋስትና ሆኗል።
አሁን ላይ አየር ኃይሉ የሀገሪቱን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ በሚያደርገው ጥረት አዲስ ምዕራፍ ላይ ደርሷል።
መንግሥት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን የዘመናዊ አየር ኃይል ፉክክር በመገንዘብ፣ ከሩሲያ መንግሥት ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት 12 የሱ-35 (Su-35) 4ኛ++ ትውልድ ተዋጊ ጄቶችን ተረክቧል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ቀዳሚ የተባለውን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታጠቁት እነዚህ ጀቶች፣ ከአየር-ወደ-አየር እና ከአየር-ወደ-ምድር የመዋጋት ከፍተኛ ብቃት አላቸው።
በተለይም ከየትኛውም አቅጣጫ የሚተኮሱ የክሩዝ ሚሳይሎችን እስከ 200 ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ አስቀድሞ የመለየት እና በአየር ላይ የማምከን አቅም አላቸው።
ይህ ርክክብ ኢትዮጵያ አየር ክልሏን ከሕገ-ወጥ ጥሰቶች በመጠበቅ የሰማይ ሉዓላዊነቷን ከማረጋገጥ ባለፈ፣ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ዘመናዊ የውጊያ ቴክኖሎጂ በመታጠቅ ቀዳሚዋ ሀገር እንድትሆን አስችሏታል።

የአየር ኃይሉ ዋነኛ ዓላማ ጥቃቶችን አስቀድሞ መከላከልና ሰላምን ማስከበር ቢሆንም፣ ሉዓላዊነትን የሚደፍር አካል ሲኖር ፈጣንና ተመጣጣኝ ምላሽ ለመስጠት ሁሌም ዝግጁ ነው።
ለዚህም ማሳያው ዘመኑን የዋጁ የጦር መሣሪያዎችን ከመጠቀም በተጨማሪ በዘመናዊ እውቀትና በዲሲፕሊን የታነጹ ብቁ አብራሪዎችን እንዲሁም የቴክኒክ ባለሙያዎችን በማፍራት ከአፍሪካ ተመራጭና ቀዳሚ ሆኖ መገንባቱ ነው።
የኢትዮጵያና የሩሲያ ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ማሳያ የሆነው ይህ የጦር ጄቶች ርክክብ፣ የሀገሪቱን ወታደራዊ አቅም ግንባታ በማሳደግ ጦርነትን ማስቀረትና ስጋቶችን በእንጭጩ መቅጨት የሚያስችል ብቃት ላይ መድረሷን በግልጽ ያረጋግጣል።
በበረከት ጌታቸው