በቴክኖሎጂና በፈጠራ አፍሪካን ግንባር ቀደም ለማድረግ ያለመ ታላቅ ዓለም አቀፍ መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

You are currently viewing በቴክኖሎጂና በፈጠራ አፍሪካን ግንባር ቀደም ለማድረግ ያለመ ታላቅ ዓለም አቀፍ መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

AMN – ሰኔ 06/2018 ዓ.ም

በአህጉሪቱ የሚስተዋሉ ፈታኝ ችግሮችን በምርምርና ቴክኖሎጂ ግኝቶች ለመፍታት አላማ ያደረገ ታላቅ ዓለም አቀፍ የምርምር ኮንፈረንስ እና የቴክኖሎጂ ውድድር በአድዋ ድል መታሰቢያ መካሄድ ጀምሯል።

በቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት አዘጋጅነት በተሰናዳው በዚህ መድረክ ላይ ከ16 የዓለም ሀገራት የተወከሉ ተመራማሪዎችና የፈጠራ ባለሙያዎች የተገኙ ሲሆን፤ 18 የምርምር ሥራዎች፣ 100 የፈጠራ ውጤቶች እና 34 የቴክኖሎጂ ግኝቶች ለዕይታና ለውድድር ቀርበዋል።

በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር) በመድረኩ መክፈቻ ላይ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት የቴክኖሎጂ ዕድገትና ሰው ሠራሽ አስተውሎ (AI) በዓለም አቀፍ ደረጃ በኢኮኖሚና በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ከፍተኛ ለውጥ እያመጡ ነው።

ለማኅበረሰባዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት የሚቻለው በመንግሥት ጥረት ብቻ ሳይሆን በወጣት ተመራማሪዎች፣ በሥልጠና ተቋማትና በፖሊሲ አውጪዎች የጋራ ጥምረት መሆኑን አስገንዝበዋል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በመድረኩ ላይ የቀረቡ የፈጠራ ሥራዎች የዓለምን ተጨባጭ ችግሮች ለመፍታት ታስበው የተዘጋጁ መሆናቸውንና ለሀገሪቱ ወጣቶችም ትልቅ የልምድ ልውውጥ ዕድል እንደሚፈጥሩ ገልጸዋል።

ከማላዊ መጥተው በመድረኩ ላይ የተሳተፉ ወጣት ተመራማሪዎች፤ ይህ መድረክ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ከመጡ ባለሙያዎች ጋር ለመገናኘትና የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ባለሀብቶች ለማስተዋወቅ ትልቅ ድልድይ እንደሆነላቸው በደስታ ገልጸዋል።

የሀገር ውስጥ ወጣት ተመራማሪዎችም ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ያላትን ደረጃ ለመለካትና ክፍተቶችን ለይቶ ወደፊት ለመራመድ መድረኩ ትልቅ አቅም እንደሚሆናቸው አመልክተዋል።

በአድዋ ድል መታሰቢያ የተጀመረው ይህ መርሃ ግብር ለሦስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ይሆናል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review