የኢትዮጵያና ሩሲያ የንግድ ልውውጥ ከ1 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር በላይ መሻገሩን ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲን ገለጹ

You are currently viewing የኢትዮጵያና ሩሲያ የንግድ ልውውጥ ከ1 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር በላይ መሻገሩን ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲን ገለጹ

AMN- ጥቅምት 19/2019 ዓ.ም

ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ታሪካዊና የቆየ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲን በድጋሚ አረጋግጠዋል።

ፕሬዚዳንቱ፣ እያደገ የመጣውን የሁለትዮሽ ንግድ፣ እየሰፋ ያለውን የኢኮኖሚ ትብብር እና በዓለም አቀፍና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን ተመሳሳይ አቋም አፅንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባጋራው ዘገባ፣ ፕሬዚዳንት ፑቲን ኢትዮጵያ በሞስኮ በተካሄደው 3ኛው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ እንዲሁም ከዚህ ቀደም በሶቺ (እ.ኤ.አ. 2019) እና በሴንት ፒተርስበርግ (እ.ኤ.አ. 2023) በተካሄዱት መድረኮች ላይ ለነበራት ንቁ ተሳትፎ አድናቆት መቸራቸውን ጠቅሷል።

ፕሬዚዳንቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን 3ኛውን የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ ለመካፈል ወደ ሞስኮ በመምጣቶ እና በዚሁ አጋጣሚ በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ በድጋሚ ለመወያየት በመቻላችን ላመሰግንዎ እወዳለሁ ማለታቸውን ዘገባው አመላክቷል።

ፕሬዚዳንቱ በሩሲያ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ወዳጅነት እና በሁለቱ ሀገራት መሪዎች መካከል የሚታየው ገንቢ ግንኙነት ለሁለቱ ህዝቦች ያለውን ታላቅ ፋይዳ አንስተዋል።

ባለፈው መስከረም ወር በኒው ዴልሂ ከተካሄደው የብሪክስ ጉባኤ ጎን ለጎን ከኢትዮጵያ መሪ ጋር ያደረጉትን ውይይት ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ፣ በወቅቱም የሁለትዮሽ ትብብር ዋና ዋና ዘርፎችን መገምገማቸውን ገልጸዋል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ ከፍተኛ እድገት ማሳየቱን የጠቆሙት ፕሬዚዳንት ፑቲን፣ የሁለትዮሽ ንግዱ በዚህ ዓመት በመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ ከ1 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር በላይ መድረሱን ይፋ አድርገዋል።

ይህ አሃዝም እ.ኤ.አ. በ2025 ከተመዘገበው አጠቃላይ መጠን በእጥፍ የሚበልጥ መሆኑን አብራርተዋል።

ሁለቱ ሀገራት የኃይል፣ የእርሻ፣ የኢንዱስትሪ፣ የሰላማዊ ህዋ ምርምር፣ የሳይንስ፣ የጤና እና የትምህርት ዘርፎችን ጨምሮ በበርካታ መስኮች ሰፊ ትብብር ለማድረግ የሚያስችሉ ተስፋ ሰጪ እድሎች እንዳሏቸውም ጠቁመዋል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ በብሪክስ እና በሌሎች ሁለገብ መድረኮች ላይ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ቅንጅት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አፅንኦት ሰጥተዋል።

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲን፣ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2027 የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን (ኮፕ 32) በብቃት እና በስኬት ለማዘጋጀት ለምታደርገው ጥረት መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review