AMN-ግንቦት 28/2018 ዓ.ም
የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት በሰራተኞች ዘንድ የአገልጋይነት እሳቤን አጎልብቷል ሲሉ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ኃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ጀማሉ ጀንበር (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
8ኛው የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ባለ 7 ወለል ህንፃ ተገንብቶ በከንቲባ አዳነች አቤቤ ተመርቆ በይፋ ሥራ ጀምሯል፡፡
በዚሁ ወቅት ጀማሉ ጀንበር (ዶ/ር) እንዳሉት፤ በከተማ አስተዳደሩ ተደራሽ እየተደረገ ያለው የመሶብ የአንድ ማእከል ዲጂታል አገልግሎት በሰራተኛው ዘንድ ያለውን የአገልጋይነት እሳቤ እንዲጎለብት አስችሏል፡፡

ወጥነት ያለው የአገልጋይ ስነ-ምግባር በመቅረፅ እንዲሁም ብልሹ አሰራርን በማስቀረት ጥራት ያለው አገልግሎት ለህዝቡ ተዳራሽ እንዲሆን እያደረገ ስለመሆኑም ሃላፊው አንስተዋል፡፡
ማእከሉ በቴክኖሎጂ ተደራጅቶ 96 ተገልጋዮችን በአንድ ጊዜ የሚያስተናግዱ መስኮቶች እንዳሉት በ22 ተቋማትና በ114 አገልግሎቶች የተደራጀ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ማእከሉ በመንግስትና ህዝብ መካከለል መተማመንን በመፍጠር ህብረተሰቡ ለከተማዋ ሁንተናዊ እድገት ጉልህ ድርሻ እንዲያበረከት ማስቻሉን ጨምረው ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም በርካታ አገልግሎቶችን ወደ የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት በማስገባት ነዋሪዎች ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎት እንዲያገኙ እናደርጋለን ብለዋል።

የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎትን በአጭር ጊዜ ውስጥ በቀሪ ክፍለ ከተሞች ተደራሽ በማድረግ ቁጥሩን 11 ለማድረስ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ተመላክቷል፡፡
አገልግሎቱ አዲስ የስራ ባህል ለውጥን በመፍጠር የስራ ባህል እንዲሻሻል ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ቴዎድሮስ ወ/ሚካኤል ናቸው፡፡
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰልቺ ከነበረው ቢሮክራሲ የሚያላቅቅ በመሆኑ ነዋሪዎች በማዕከላቱ በመገኘት መገልገል ይችላሉ ብለዋል፡፡
በሚካኤል ህሩይ