በአዲስ አበባ የ70 ግራም ዳቦ የመሸጫ ዋጋ 13 ብር እንዲሆን ተወሰነ

You are currently viewing በአዲስ አበባ የ70 ግራም ዳቦ የመሸጫ ዋጋ 13 ብር እንዲሆን ተወሰነ

AMN- ጥቅምት 19/2019 ዓ.ም

የ70 ግራም ዳቦ የመሸጫ ዋጋ 13 ብር እንዲሆን መወሰኑን የአዲስ አበባ ከተማ ዳቦ አምራች ነጋዴዎች ማህበር አስታወቀ፡፡

የመሰረታዊ የፍጆታ ምርቶችን አቅርቦት በማብዛት በሻጭ እና በገዥ መካከል ጤናማ የንግድ ትስስር ለመፍጠር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በትኩረት እየሰራ ይገኛል፡፡

የዳቦ ጥራት፣ አቅርቦት እና ዋጋን ለማስተካከል የንግዱ ማህበረሰብ ሲመክር ቆይቶ፣ አሁን ላይ የ70 ግራም ዳቦ በ13 ብር ይሸጥ ዘንድ ዋጋ መቆረጡን ከአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ዳቦ አምራች ነጋዴዎች ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሁሴን ላለምዳ ተናግረዋል፡፡

የዳቦ ግራም በሚቀንሱ የዳቦ አምራቾች እና ዳቦ ቤቶች ላይ ማህበሩ ከፍተኛ ቁጥጥር እንደሚያደርግ ያመለከቱት አቶ ሁሴን፣ በዚህ ድርጊት ላይ የሚሳተፉ አካላት በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ይሰራል ብለዋል፡፡

አክለውም በከተማዋ ሁሉም አካባቢዎች የዳቦ አቅርቦትን አስተማማኝ ለማድረግ እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡

“የንግዱ ማህበረሰብ የህብረተሰቡ አንድ አካል ነው” ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ ህገ-ወጥ የዋጋ ጭማሪን፣ የጥራት መጓደልን እና የኪሎ መቀነስ ችግርን ለመከላከል ሁሉም ቅን እና ተባባሪ ሊሆን እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ይህ የዋጋ ውሳኔ የመንግስት ዳቦ አምራቾችን እና አቅራቢዎችን እንደማይመለከት የጠቆሙት አቶ ሁሴን፣ የግል ዳቦ አምራቾች እና አቅራቢዎች ግን የ70 ግራም ዳቦ የመሸጫ ዋጋ 13 ብር ብቻ እንዲሆን መወሰኑን አብራርተዋል፡፡

የመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎችን አቅርቦት ማሳደግ ፣ አማራጭ ገበያዎችን ማስፋት እና ቁጥጥርን ማጠናከር ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በትኩረት መስራቱን ቀጥሏል፡፡

በተመስገን ይመር

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review