በአዲስ አበባ ድንገተኛ የበካይ ጋዝ ልኬት ከተደረገባቸው ተሽከርካሪዎች 44 ነጥብ 5 በመቶዎቹ መስፈርቱን አላሟሉም

You are currently viewing በአዲስ አበባ ድንገተኛ የበካይ ጋዝ ልኬት ከተደረገባቸው ተሽከርካሪዎች 44 ነጥብ 5 በመቶዎቹ መስፈርቱን አላሟሉም

AMN-ጥቅምት 19/2019 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ ድንገተኛ የበካይ ጋዝ ልኬት ከተደረገባቸው 200 ተሽከርካሪዎች መካከል 44 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆኑት የተቀመጠውን መስፈርት ሳያሟሉ መገኘታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው የተሽከርካሪዎች በካይ ጋዝ ልቀት መጠን እና የቅነሳ ስልቶችን አስመልክቶ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብር አካሂዷል።

በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የበካይ ጋዝ ልቀት ድንገተኛ ፍተሻ ከተደረገባቸው ተሽከርካሪዎች መካከል 44 ነጥብ 5 በመቶ ያህሉ ዓለም አቀፍ መስፈርቱን ሳያሟሉ መቅረታቸውን የገለጸው ቢሮው፤ ከፍተኛውን በካይ ጋዝ የሚለቁት የናፍጣ ተሽከርካሪዎች መሆናቸውን አስታውቋል።

የቢሮው የሞተር አልባ ትራንስፖርት ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ግርማ ሳሙኤል እንደገለጹት፤ በምርመራው ከተካተቱት 200 ተሽከርካሪዎች ውስጥ 111ዱ የቤንዚን፣ 89ኙ ደግሞ የናፍጣ ናቸው።

ከእነዚህም ውስጥ ከቤንዚን ተሽከርካሪዎች 101ዱ መስፈርቱን ሲያሟሉ፣ ከናፍጣ ተሽከርካሪዎች ግን ማለፍ የቻሉት 13ቱ ብቻ እንደሆኑ ገልጸዋል።

ተሽከርካሪ አሮጌ ስለሆነ ብቻ በካይ ጋዝ ይለቃል ማለት እንዳልሆነ ጠቁመው ፣ ዋናው ጉዳይ የተሽከርካሪው አያያዝና የጥገና ሁኔታ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

የተሽከርካሪዎች ጭስ በሰውና በአካባቢ ጤና ላይ እያስከተለ ያለው ጉዳት እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ ቢሮው በቀጣይ ጥብቅ እርምጃ እንደሚወስድ አሳስቧል።

ወንድምአገኝ አበበ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review