የኢነርጂ ቅየራ ከትራንስፖርት አገልግሎት ባሻገር ለኢንዱስትሪዎች ትልቅ አበርክቶ አለው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing የኢነርጂ ቅየራ ከትራንስፖርት አገልግሎት ባሻገር ለኢንዱስትሪዎች ትልቅ አበርክቶ አለው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN- ጥቅምት 20/2019 ዓ.ም

የኢነርጂ ቅየራ ለትራንስፖርት አገልግሎት ብቻ ሳይሆን ለሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎችም ትልቅ አበርክቶ እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከነዳጅ ወደ ተፈጥሮ ጋዝ የተለወጡ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶችን ሥራ ባስጀመሩበት ወቅት እንደገለጹት፣ የኢነርጂ ቅየራ ሥራዎች የዜጎችን የኑሮ ጫና ለማቃለልና የሀገር ውስጥ ኢኮኖሚን ለማጠናከር ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው አንስተዋል።

የጋዝ ልማት ለኢንዱስትሪዎች ትልቅ ግብዓት እንደሚሆን ጠቁመው፣ ለአብነትም የሞጆ እና የደብረ ብርሃን ሴራሚክ ማምረቻ ፋብሪካዎች ሙሉ በሙሉ ወደ ጋዝ ኢነርጂ መሸጋገራቸውን አብራርተዋል።

ሽግግሩ ፋብሪካዎቹ በውድ ዋጋ ይፈጽሙት የነበረውን የውጭ ነዳጅ ግዥ እንደሚያስቀርላቸውና በሀገር ውስጥ ርካሽ ኢነርጂ ስለሚያመርቱ ምርቶቻቸው በተመጣጣኝ ዋጋ ለሕዝብ እንዲቀርቡ እንደሚያስችላቸውም ገልጸዋል።

ይህም በግንባታ ወጪዎችና በቤት ዋጋ ላይ አዎንታዊ ለውጥ በማምጣት የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠርና የውጭ ምንዛሬ ፍላጎትን ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል።

የመንግሥት መለያ፣ ቃል ኪዳኑን በተግባር መፈጸም እንዲሁም የጀመራቸውን ሥራዎች ጥራትና ፍጥነት ጠብቆ ለፍጻሜ ማብቃት መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የኢነርጂ ማመንጫዎች በማስፋት የሀገር ውስጥ አቅምን ማጠናከር እንደተቻለ ተናግረዋል።

የሀገር ግንባታ ሂደት ረጅም እና ትዕግሥት የሚጠይቅ መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሕዝቡ እነዚህን ጅምር ውጤቶች በመጠቀምና በመደገፍ ለቀጣይ ሥራዎች አጋር እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።

ሀገር በአንድ ጀምበር አትገነባም፣ ነገር ግን በጋራ በመትጋት፣ በመተባበርና ተስፋን ሰንቆ በመሥራት የነገ ሀገር ተረካቢ ልጆችን ጊዜ ብሩህ ለማድረግ ዛሬ መትጋትን ይጠይቃል ብለዋል፡፡

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review