AMN- መስከረም 17 /2019 ዓ.ም

ኢትዮጵያ በርካታ ሐይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት በድምቀት የሚከበርባት አፍሪካዊት ሃገር ስትሆን፤ አብዛኞቹ በዓላት በአብሮነት፤ በወንድማማችነትና በጋራ የሚከበሩ መሆናቸው ደግሞ ልዩ ያደርጋቸዋል፡፡
እንደ እንቁጣጣሽ፤ መስቀል ደመራ፣ ኢሬቻ፣ ኢድ አል አድሃ/አረፋ፣ መውሊድ፤ ጥምቀት፤ አሸንዳ፣ ሻደይ፣ ሶለል፣ ጎቤ፤ ሽኖዬ፤ ጊፋታ፣ ፊቼ ጨምበላላ፣ ዮ-ማስቃላ፤ ደራሮ፤ ጋዜ መስቃላ፤ ድሽታ ግና፤ ያሆዴ፤ ጓንዷ፤ማሽቃሮ እና ሌሎች በርካታ ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት በቤተሰብ እና በአደባባይ የሚከበሩ ናቸው፡፡

እነዚህ በዓላት በአብዛኛው በጋራ የሚከበሩ በመሆናቸው ጎረቤት ከጎረቤቱ፤ ዘመድ ከአዝማዱ፤ ጓደኛ ከወዳጁ ጋር ተጠራርቶ በጋራ ያከብራል፡፡
በበዓል ወቅት ወደ ቤተሰብና ዘመድ ሄዶ በዓሉን በጋራ ማክበር የተለመደ ባህል ሲሆን በርካቶችም ዕለቱን ለማክበር ከዉጭ ሃገራት ጭምር ወደ ተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎችና ወደ ቤሰተቦቻቸዉ ይጓዛሉ፡፡
በበዓላቱ አከባበር ስነ ስርዓት ላይ ባህላዊ ምግብና መጠጦች ይቀርባሉ፤ ታዳሚዎቹም እንደ ሐይማኖትና ባህላቸው የተለያዩ አልባሳትን ይለብሳሉ፤ ሐይማኖታዊና ባህላዊ ጭፈራዎች፤ ውዝዋዜዎች እና ዜማዎች ይደመጣሉ፡፡
በአብዛኞቹ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ሃይማኖቶች ዘንድ በዓልን በጋራ ማክበር ትልቅ እርካታንና ደስታን የሚሰጥ ሲሆን በአልን ለብቻ ማክበር የብቸኝነት ስሜትን ሊፈጥር ይችላል፡፡

ሃይማኖታዊም ሆነ ባህላዊ በዓላቱ በሚከበሩበት ወቅት የየራሳቸዉ የአካባበር ሥነ ሥርዓት ያላቸዉ ሲሆኑ በአብዛኞቹ አከባበሮች ላይ በተለያዩ ምክንያቶች የተጣሉ ግለሰቦች ይታረቃሉ፤ እርቅና ሰላምም ይወርዳል፡፡
እርስ በርስ ተጣልቶ ወይም ቂም ይዞ በዓልን በጋራ ማክበር የማይፈቀድና የማይመከር ሲሆን ፈጣሪ የሚታረቀን እኛ ስንታረቅ ነዉ የሚል የየራሳቸዉ አስተምህሮትና ባህላዊ እሴት አላቸዉ፡፡
በአብዛኞቹ በዓላት ላይ በስፋት ከሚተገበሩ ሥነ ሥርዓቶች መካከል የተቸገረን መርዳት፤ ቤት ካፈራዉ ላይ ተቋድሶ መብላት፤ መተሳሰብና መተጋገዝ የተለመደ ባህል ሲሆን አንዳንድ ሃይማኖቶችና ባህሎች ይህንን ሥነ ሥርዓት እንደ አስገዳጅ ህግ ይወስዱታል፡፡
በበዓላት ወቅት መልካም ምኞትን መግለጽ፤ ስጦታን መለዋወጥ፤ በአካልም ሆነ በስልክ ደዉሎ መጠያየቅ፤ አብሮ መዝናናትና መሰል ሥነ ሥርዓቶችን መፈጸምም የተለመደ ነዉ፡፡
ከዘመናዊው ዓለም ኑሮ፤ ከሥራና ከርቀት ጋር ተያይዞ ወደ ቤተሰብ ሄደው በዓሉን ለማክበር የማይችሉት ደግሞ የተለያዩ መገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ይጠያየቃሉ፤ የብቸኝነት ስሜት እንዳይሰማቸዉ ያደርጋሉ፡፡
የኢትዮጵያዊያን የበዓላት አከባበር እጅግ ጥልቅ ባህላዊና ሃይመኖታዊ እሴቶች ያላቸዉ ሲሆኑ ማህበራዊ ህይወትን፤ ወንድማማችነትንና አብሮነትን ያጠናክራሉ፤ ልዩነቶችንና ቅራኔዎችን ይፈታሉ፤ እርቅና ሰላምን ያወርዳሉ፤ በምረቃና ምስጋና የማይረሱና ለዘመናት የሚታወሱ ስሜቶችን ይፈጥራሉ፡፡
ቄጤማዉ፤ እጣንና ሰንደሉ፤ የበጉና የዶሮዉ ጩህት፤ ችቦና መብራቱ፤ ጨዋታና ሳቁ በየበዓላቱ የሚስተዋሉ ድባቦች ናቸው፡፡
ስለ በዓል አከባበር ያለዎትን ገጠመኝ ያጋሩን!
መልካም የመስቀል በዓል!
በወንድማገኝ አሰፋ