AMN – ሕዳር 1/2019 ዓ.ም
የዘንድሮው የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ 31) “ጉዞ ወደ ዘላቂ፣ አይበገሬነት እና ፍትሃዊነት ወደ ተረጋገጠበት መጻኢ ዘመን” በሚል መሪ ሀሳብ በቱርክ አንታሊያ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በጉባዔው ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ተሳታፊዎች፣ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ያስመዘገበችው ውጤት ለአፍሪካ ሀገራት ትልቅ አርአያ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎችን ለመቋቋም፣ አካባቢን ከአረንጓዴ ልማት ጋር ለማስተሳሰር እና የንጹህ ሃይል ማመንጫዎችን እውን ለማድረግ የምታደርጋቸው ጥረቶች አበረታች መሆናቸው በሰፊው ተነስቷል።
የሞዛምቢክ የግብርና፣ የአካባቢ ጥበቃ እና የዓሣ ሀብት ሚኒስቴር ተወካይ ሉዊስ ንያሙሽ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ያልተያዘች ታሪካዊ ሀገር ከመሆኗ ባሻገር በፓን-አፍሪካኒዝም፣ በአረንጓዴ አሻራ እና በከተሞች ግንባታ ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተች ትገኛለች።

አያይዘውም፣ ሀገሪቱ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሯ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት በማረጋገጥና ተግዳሮቶችን ወደ ውጤት በመቀየር ረገድ ላሳየችው ቁርጠኝነት አፍሪካ እና የበለጸጉ ሀገራት ጭምር ሊማሩበት እንደሚገባ ገልጸዋል።
የዓለም ባንክ የቀጣናዊ የአየር ንብረት አይበገሬነት ፕሮግራም (RCRP2) የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያ ዩቮን ሱንዱ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 56 ቢሊዮን ዛፎችን መትከልና ማጽደቅ መቻሏን አድንቀዋል።
አክለውም እንደ ማላዊ ያሉ ሀገራት ከአየር ንብረት አደጋዎች ለመላቀቅ ከኢትዮጵያ ልምድ መውሰድ እንደሚገባቸው ጠቁመዋል፡፡

ሀገሪቱ በሃይድሮ ኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ መስክ 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ የሚያመነጨውን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እውን በማድረግ በራስ አቅም እንዴት መለማት እንደሚቻል ማሳያ በመሆኑ፣ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ይህንን ተሞክሮ መቅሰምና ማስፋት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በቱርክ ሀበርቱርክ ቲቪ (Habertürk TV) የዜና ዘጋቢ ኤምሬ ካራቻ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎችን በአዎንታዊ መልኩ በመምራት አርአያነት ያላቸውን ስራዎች ማከናወኑን ጠቅሰዋል።
አፍሪካውያን አዎንታዊ ተሞክሮዎችን በመቅሰም ወደ ተግባር መሸጋገር እንዳለባቸው ገልጸው፣ በመጪው ኮፕ 32 (COP32) ጉባኤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ምድር ስኬታማና በተግባር የተደገፈ ታሪካዊ ጉባኤ እንደምታዘጋጅ ትልቅ እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

የዓለም ሀገራት እና መሪዎችም የኢትዮጵያን ተሞክሮ በመቅሰም በሀገራቸው ሊተገብሩት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በበረከት ጌታቸው
#EthiopiaAtCOP31 #COP31 #GreenDevelopment #ClimateActionAfrica #COP32 #addismedianetwork #Ethiopia #addisababa