ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አርንጓዴ ልማትን በመገንባት ለአለም ሃገራት ተምሳሌት ሆናለች

You are currently viewing ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አርንጓዴ ልማትን በመገንባት ለአለም ሃገራት ተምሳሌት ሆናለች

AMN- ኅዳር 2/2019 ዓ.ም

አለማችን በአየር ንብረት ለዉጥ ምክንያት በርካታ ጉዳቶችን በማስተናገድ ላይ ትገኛለች፡፡

ተደጋጋሚ ድርቅ፤ ያልተጠበቀ የጎርፍ አደጋ፤ ከፍተኛ የአየር ሙቀት፤ አዉሎ ነፋስ እና የባህር ወለል ከፍታ መጨመር በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች ከሚከሰቱት አደጋዎች መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸዉ፡፡

የአፈር ለምነትና የዉሃ አቅርቦት መቀነስ፤ የተመጣጠነ የምግብ እጦት፤ የድህነት መባባስ እና መሰል ጉዳቶችም ከዚሁ ከአየር ንብረት ለዉጥ የሚመነጩ ተዛማጅ ተግዳሮቶች ናቸዉ፡፡

ኢኮኖሚያቸዉ በግብርና ላይ የተመሰረተ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አዳጊ ሃገራት ዋንኛ የአየር ንብረት ለዉጥ ገፈት ቀማሾች ሲሆኑ በምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ሂደታቸዉ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ በማሳደር ላይ ይገኛል፡፡

የአየር ንብረት ለዉጥ ተጽእኖ ሁሉንም የአለም ሃገራት የሚጎዳ ችግር ቢሆንም ተጽእኖዉን ለመከላከል የሚወሰደዉ እርምጃ የተለያየ መሆኑ ደግሞ በተግባራዊ መፍትሄዉ ላይ ትልቅ ተግዳሮትን ፈጥሯል፡፡

በአየር ንብረት ተጽእኖ ከመጎዳት ይልቅ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ መስጠትን ቀዳሚ አጀንዳዋ ያደረገችዉ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የደን መመናመንን በመዋጋት ላይ ትገኛለች፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በተጀመረዉ በዚህ መርሃ ግብር 56.8 ቢሊዮን ችግኞችን መትከል የተቻለ ሲሆን የሀገሪቱን የደን ሽፋን በፊት ከነበረበት 17.2 በመቶ አሁን ወደ 23.6 በመቶ ከፍ ማድረግ ተችሏል፡፡

በአንድ ሄክታር መሬት ላይ ይደርስ የነበረውን 130 ቶን የአፈር መሸርሸር ወደ 54 ቶን ዝቅ ማድረግ የተቻለ ሲሆን ደርቀው የነበሩ የውሃ አካላት እንዲያገግሙና የውሃ መጠናቸው እንዲጨምር ትልቅ ሚና ተጫውቷል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በኢኮኖሚው ዘርፍም አዎንታዊ ለውጦችን እያስመዘገበ የሚገኝ ሲሆን የቡና እና የሆርቲካልቸር ዘርፍ የወጪ ንግድ ገቢ እንዲጨምር አድርጓል፡፡

በእርሻ ልማት ዘርፍ ምርታማነት እንዲያድግ፣ የሌማት ትሩፋት ፕሮግራም ከደን ልማት ጋር በመተሳሰሩ በከብት እርባታ፣ በንብ ማነብ፣ በዶሮ እርባታና በዓሳ ልማት አበረታች ውጤት እንዲመዘገብ ትልቅ አስተዋጾ አበርክቷል፡፡

ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አርንጓዴ ልማትን በመገንባት አለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን በመከላከል አዎንታዊ አስተዋፅዖ እያበረከተች ትገኛለች፡፡

ሃገሪቱ የአየር ንብረት ተጽእኖዉን ለመከላከል እያደረች ባለዉ ጠንካራ ጥረት 32ኛውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን ለማዘጋጀት እንድትመረጥ አስችሏታል፡፡

31ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 31)“ጉዞ ወደ ዘላቂ፣ አይበገሬነት እና ፍትሃዊነት ወደተረጋገጠበት መጻኢ ዘመን” በሚል መሪ ቃል በቱርኪዬ አንታሊያ እየተካሄደ የሚገኘዉ ሲሆን ኢትዮጵያም በጉባዔዉ ላይ መሳተፍና የራሷን ፓቪሊዮን በመክፈት ልምዶቿን በማካፈል ላይ ትገኛለች፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢኒሼቲቭ የሆነው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፣ ከ90 በመቶ በላይ የደረሰው ንጹህ የሃይድሮ ኢነርጂ አጠቃቀም፣ የኤሌክትሪክ መኪናዎችን ለማበረታታት የተወሰዱ እርምጃዎች እና በግብርናና ከተማ ልማት የተከናወኑ ተግባራት ዓለም አቀፍ እምነትና አድናቆት እያተረፉ ይገኛሉ፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review