ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ለመጻኢ ተግዳሮቶች ቀድማ መፍትሔ በማስቀመጥ የሚጠበቅባትን ድርሻ እየተወጣች መሆኑን አመልክተዋል – ቢልለኔ ስዩም

You are currently viewing ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ለመጻኢ ተግዳሮቶች ቀድማ መፍትሔ በማስቀመጥ የሚጠበቅባትን ድርሻ እየተወጣች መሆኑን አመልክተዋል – ቢልለኔ ስዩም

AMN ኅዳር 2/ 2019

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ለመጻኢ ተግዳሮቶች ቀድማ መፍትሔ በማስቀመጥ ተጨባጭ እርምጃዎችን በመውሰድ የሚጠበቅባትን ድርሻ እየተወጣች መሆኑን አመልክተዋል ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬተሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ገለጹ።

31ኛው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP31) አስመልክቶ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬተሪያት መግለጫ ሙሉ ቃል።

በቱርክዬ አስተናጋጅነትና በአውስትራሊያ የድርድር መሪነት የሚካሄደው 31ኛው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP31) በጥቅምት 30 ቀን 2019 ዓ.ም በቱርክዬ አንታሊያ የተጀመረ ሲሆን፣ ይህንኑ ተከትሎ የሚካሄደው የመሪዎች ጉባኤም ዛሬ ኅዳር 2 ቀን 2019 ዓ.ም በይፋ ተጀምሯል።

‎የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመሪዎች ጉባኤው ለመሳተፍ ከመክፈቻው አንድ ቀን ቀደም ብለው ቱርክዬ የተገኙ ሲሆን፣ በዋዜማውም ከቱርክዬ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ረጅብ ጣይብ ኤርዶጋን ጋር ፍሬያማ ውይይት አካሂደዋል።

በውይይታቸውም በሁለቱ ሀገራት መካከል ባለው ጠንካራ አጋርነት ላይ በመመሥረት የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ስለሚያስችሉ ዕድሎች፣ ኢትዮጵያ የኮፕ32 ፕሬዚዳንትነትን ለመረከብ በምታደርገው ዝግጅት ረገድ ስለሚኖረው አጋርነት፣ እንዲሁም የወል ትኩረት በሚሹ ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ስለሚኖሩ የትብብር ዕድሎች ተወያይተዋል።

‎ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመሪዎች ጉባኤ ቆይታቸውም ከባርቤዶስ፣ ፊንላንድ፣ ኖርዌይ፣ ኢራቅ፣ ሶማሊያና ቦትስዋና መሪዎች፣ እንዲሁም ከኳታር አሚር ጋር ፍሬያማ የሁለትዮሽ ውይይቶችን አካሂደዋል።

ውይይቶቹም የሁለትዮሽ ትብብሮችን ይበልጥ ማጠናከር፣ የጋራ የአየር ንብረት ለውጥ ተግዳሮቶችንና እየተወሰዱ ያሉ ምላሾች፣ በታዳሽ ኃይል ዘርፍ የሚደረጉ ኢንቨስትመንቶች፣ የጋራ የልማት አቅምን ማጎልበት፣ ቀጣናዊ ሰላምና ተጠቃሚነት፣ አህጉራዊውን የአየር ንብረት አጀንዳ ማጠናከር እንዲሁም ወደ COP32 በሚደረገው ጉዞ ሊኖሩ በሚችሉ የትብብር ዕድሎች ላይ ያተኮሩ ነበሩ።

‎ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመሪዎች ጉባኤው መክፈቻ ላይም ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ የአረቢካ (ኢትዮፒካ) ቡና መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ በሙቀት መጨመርና በዝናብ ሁኔታ ላይ በሚታዩ ለውጦች ምክንያት ደኖቿና የእርሻ መሬቶቿ ለአደጋ የተጋለጡበትን ወቅቶች በማንሳት፤ ይሁን እንጂ በመደመር ፍልስፍና እና በብሔራዊ ተሳትፎ በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በአንድነት 56 ቢሊዮን ችግኞችን መትከላቸውን አስረድተዋል።

ይህም የተጎዱ መሬቶችን መልሶ ለማልማትና የደን ሽፋንን ለማስፋፋት ከማገዙም በላይ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድሎችን እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

‎በተጨማሪም የኢትዮጵያ ዋነኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ምንጭ ውኃ መሆኑን አስረድተው፣ ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ሽግግር በማድረግ የነዳጅና የናፍጣ መኪናዎችን ማስመጣት መከልከሏን ጠቅሰዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ለመጻኢ ተግዳሮቶች ቀድማ መፍትሔ በማስቀመጥ ተጨባጭ እርምጃዎችን በመውሰድ የሚጠበቅባትን ድርሻ እየተወጣች መሆኑን አመልክተዋል።

‎ኢትዮጵያ COP32ን የምታስተናግድ ሀገር መሆኗን በማንሳትም፣ ቅድመ እርምጃን ማዕከል ያደረገ አካሄድ ለመከተል፣ የማስጠንቀቂያ ምልክቶች በሚታዩበት ወቅት የገንዘብ ድጋፍ ወዲያውኑ እንዲለቀቅና ከፍተኛ ተጋላጭነት ላይ ለሚገኙ ማኅበረሰቦች በቅድሚያ እንዲደርስ ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።

ለዚህም ኢትዮጵያ የCOP31ን ውጤታማነት ለማረጋገጥ ከሚመለከታቸው ጋር በቅርበት እንደምትሠራ አስገንዝበዋል።

‎በመጨረሻም የዓለም መሪዎችና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በCOP32 በምድረ ቀደምቷ ኢትዮጵያ እንዲገናኙ ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ ቀጣዩን ኮፕ32 ለማዘጋጀት በምትሰናዳበት በዚህ ወቅት፣ ይህ ጉባኤ በርካታ ዓለም አቀፍ ትብብሮችን ለመፍጠር፣ አጋርነቶችን ለማጠናከር፣ ተሞክሮዎችን ለመቅሰም እና የሀገሪቱን በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የምታከናውነውን እርምጃ መሪነት ለማረጋገጥ አስቻይ መድረክ ነው።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review