AMN-ኅዳር 2/2019 ዓ.ም
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በአፍሪካ አንደኛ የሆነውን ስሙን ፣ በዓለም ቁጥር አንድ የጎዳና ላይ ሩጫ ሆኖ እንዲመዘገብ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።
26ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪሎ ሜትር የ2019 የባንክ ኦፍ አሜሪካ ሩጫ ህዳር 13 ቀን 2019 ዓ.ም 60 ሺህ ሯጮች በሚገኙበት በድምቀት እንደሚደረግ የውድድሩ አዘጋጆች ገልጸዋል።
የታላቁ ሩጫ አዘጋጅ ህሊና ንጉሴ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ እንደገለጹት ፤ ውድድሩ በአፍሪካ ቁጥር አንድ ነው ፤ ነገር ግን አሁን ላይ በዓለም አንደኛ ደረጃ ለማስመዝገብ የተሳታፊዎች እና የውድድር ጥራቱን ከፍ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ውድድር የስፖርት ቱሪዝምን ለማስፋፋት ፣ ዓለም አቀፍ አትሌቶችና ጎብኚዎችን ወደ ሀገራችን ለመሳብ እንዲሁም የኢትዮጵያን ብሎም የመዲናዋ አዲስ አበባን ስም ከፍ ለማድረግ ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።
ታላቁ ሩጫ ዘንድሮ ለየት ባለ መልኩ ሦስት አይነት መነሻዋች እንደሚኖሩት አዘጋጇ ገልጸዋል። የውድድሩ ተሳታፊዎችን ፍሰት ለመጠበቅ በሦስት የተለያዩ የመነሻ ምድቦች ተከፋፍሎ ሩጫው ይከናወናል።

ቀይ ምድ በ22 መስመር ፣ አረንጓዴ ምድብ በጊዮን መስመር እንዲሁም ቢጫው ምድብ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሚሳተፉ 5 ሺህ ተማሪዎች ተዘጋጅቷል። ተማሪዎቹ “ትንሹ ኃይሌን” ለመፍጠር እና የውድድር እድል ለማመቻቸት በነፃ ይሳተፋሉ ተብሏል።
ከዚም በተጨማሪ የበጎ አድራጎት እና የማህበራዊ አገልግሎት ስራዎች የሚተገበሩበት የዘንድሮው ውድድር 8 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዷል። በሴቶች እና ህፃናት ሚኒስቴር ጠቋሚነት የተመረጡ ሦስት የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ድጋፍ ያገኛሉ።
አለምፍሬ ፒንክ ሀውስ የካንሰር ፋውንዴሽን ፣ ማረፊያ የአረጋውያን በጎ አድራጎት ማህበር እና ፍቅር ኢትዮጵያ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ህፃናት መርጃ ድርጅት ድጋፍ እንዲያገኙ የተመረጡ የበጎ አድራጎት ተቋማት ናቸው።
በአንዱዓለም ስማቸው