AMN- ኅዳር 7/2019 ዓ.ም
የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ለአንድ ሀገር ከሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በላይ የሀገር ገጽታን በመገንባት ረገድ ያለው ሚና የላቀ ነው፡፡
እንደ ፈረንሳይ፣ ስፔን፣ ታይላንድ እና ቱሪክ ያሉ ሀገራት ለዘርፉ በሰጡት ልዩ ትኩረት በየዓመቱ በሚሊየን የሚቆጠሩ ቱሪስቶችን ከመላው ዓለም ይቀበላሉ፡፡
ሀገራቱ ከጎብኚዎች ከሚያገኙት ገቢ በተጨማሪ፣ የሀገራቸውን መልካም ገጽታ ያስተዋውቁበታል፡፡
ኢትዮጵያም በአፍሪካና በዓለም ላይ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪ የሚሆኑ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ጸጋዎች ካላቸው ሀገራት ቀዳሚዋ ብትሆንም፣ ከዘርፉ በሚገባት ልክ አልተጠቀመችም፡፡
ዘርፉ በሀገር ኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን የላቀ ድርሻ አለመገንዝብ ዋንኛው ውስንነት ሲሆን፣ የቱሪስቶችን ፍላጎት አለመረዳትና መዳረሻ ቦታዎችን ምቹ አለማድረግ ደግሞ ሌላኛው ተግዳሮት ነው፡፡
በርካታ የዓለም ቱሪስቶችን እና ቢሊየን ዶላሮችን መሳብ የሚችሉ የሀገሪቱ ባህላዊ እና የተፈጥሮ ዕንቁዎች ተደብቀው፣ ታሪኮቿም አቧራ ለብሰው ለዘመናት ተቀምጠዋል፡፡

ኢትዮጵያ ያላትን የቱሪዝም ጸጋዎች በአግባቡ አሰባስባ ወደ ተደራጀ ብሔራዊ አቅም ከቀየረችው ብልጽግናዋን እውን ማድረግ እንደምትችል የተረዳው የመደመር መንግሥት፣ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
በአዲስ አበባ የተጀመረው የፓርክ ግንባታ ወደ መላው የሀገሪቱ ክፍሎች የተዳረሰ ሲሆን፣ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ የቱሪዝም ጸጋዎቿንም በመግለጥ ላይ ይገኛል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሰው ዘር መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ፣ ያሏትን ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ተፈጥሮአዊ እና ሃይማኖታዊ ቅርሶችን ለመጎብኘት የሚመጡ የውጭ ሀገራት ዜጎች ቁጥር በእጅጉ ጨምሯል፡፡
የቱሪስቶችን ፍላጎት ማሟላት የሚችሉ ዘመናዊ አየር መንገዶች፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች እየተሟሉ መምጣታቸውም የቱሪስቶች ቁጥር እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል፡፡
የጎብኚዎችን ደህንነት የሚያረጋግጡ ስራዎች መሰራታቸው፣ ለቱሪስቶች ቀላል እና ፈጣን የቪዛ አገልግሎት መመቻቸቱ እና የተለያዩ ሚዲያዎች ኢትዮጵያ ያላትን ገጽታና መስህቦች ለተቀረው ዓለም ማስተዋወቃቸውም ዘርፉ ከጸጋነት ወደ ሀገራዊ አቅም እንዲለወጥ ምቹ መደላድልን ፈጥሯል፡፡
ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከ1 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ጎብኚዎችን በማስተናገድ 5 ቢሊየን ዶላር ገቢ ማግኘቷም የኢንዱስትሪውን ውጤታማነት ያረጋግጣል፡፡
በኮንፍረንስ ቱሪዝም ረገድም 220 ዓለም አቀፍ ጉባዔዎችን በማዘጋጀት የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ለተቀረው ዓለም ማስተዋወቅ ተችሏል፡፡
አዳዲስ መዳረሻዎችም በማልማት ጭምር የቱሪዝም ኢንዱስትሪው በእጅጉ እየተነቃቃ መምጣቱ ብሔር ብሔረሰቦች ያላቸውን የተፈጥሮ ጸጋ፣ ባህልና ቅርስ ለማስተዋወቅ፣ ባህላዊ ምግብ፣ አለባበስ፣ ጭፈራና ሌሎች የማይዳሰሱ ሃብቶቻቸውን ወደ ጠንካራ ሀገራዊ ኢኮኖሚ ለመለወጥ አስችሏቸዋል፡፡
የመደመር መንግሥት በዘርፉ የሚያከናውናቸው የቱሪዝም ልማት ስራዎች አዳዲስ ሃብቶችን ከነባሩ ጋር ያያዘ መሆኑ ደግሞ፣ ሀገሪቱ በመፍጠንና በመፍጠር መርህ ከቱሪዝም ማዕድ ተቋዳሽ እንድትሆን አስችሏታል፡፡
የቱሪዝም መዳረሻዎችን ጨምሮ በኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ ልማት እየተሰሩ ያሉ ስራዎችም፣ ሀገሪቱ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንድትሆን ትልቅ አቅም እየፈጠሩላት ይገኛሉ፡፡
በእያንዳንዱ ወረዳዎች የሚገኙ የቱሪዝም ሃብቶችን እና እምቅ አቅሞችን መለየት፣ ማልማት፣ ማስተዋወቅና ማንበር ከተቻለ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ቱሪዝም ዋንኛ ምሶሶ ሆኖ መቀጠል ይችላል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ