AMN-ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም
ሁለተኛው የኢትዮ-እስራኤል ኢኖቬሽን ሳምንትን የከፈቱት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ የኢትዮጵያን የፈጠራ ገጽታ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር አለም አቀፍ ትብብር ያለው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
“ኢትዮጵያ በአዲስ የፈጠራ ዘመን ገደል ላይ ትገኛለች”ያሉት ሚኒስትሩ ለዚህም ቴክኖሎጂን ለመቀበል የሚጓጓ ወጣት ፣ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ስታርትአፕ እና አካባቢን ለማሳደግ ቁርጠኛ የሆነ መንግስት በቅንጅት ለፈጠራ አመች፣ ለለውጥ ዝግጁ ሁኔታ ላይ እንገኛለን ብለዋል።
እስራኤል በአስደናቂ የስታርትአፕ ባህሏ እና በቴክኖሎጂ እድገቷ ትታወቃለች ያሉት ሚኒስትሩ የእስራኤል የፈጠራ ሞዴል ለኢትዮጵያ ትምህርት ሰጭ በመሆኑ የትብብር ማዕቀፍ በመመሥረት በጋራ፣ ሃሳቦች የሚያብቡበት፣ ስታርትአፖች የሚበለፅጉበት፣ ቴክኖሎጂ ለኢኮኖሚ ልማት ማበረታቻ የሚሆንበትን ሁኔታ መፍጠር እንችላለን ብለዋል።
በዝግጅቱ ላይ በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ንጉሴ፤ በዓለም ላይ ስኬታማና ግንባር ቀደም የፈጠራ እና ስታርትአፕ ሥነ-ምህዳርን በማቋቋም እንዲሁም በመንከባከብ ሀገራቸው ያላትን ልምድ በዚህ ፕሮግራም ለኢትዮጵያ የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚያጋሩ አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በተፍጥሮ ሃብትና በሰው ሃይል የታደለች መሆኗን የገለጹት አምባሳደሩ ይህንን ሀብት በቴክኖሎጂ እና በኢኖቬሽን በመደገፍ ለኢኮኖሚ እድገት ለመጠቀም የሚደረገውን ጥረት ሀገራቸው እንደምታግዝም ተናግረዋል።
በዝግጅቱ ላይ በስታርትአፕ ስነ ምህዳር ግንባታ፣ በኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ፣ በታለንት ልማት እና ትምህርት፣ በግንባታ ቴክኖሎጂና ሽግግር ላይ እስራኤል ያላት ተሞክሮ በሉእካን ቡድኑ ቀርቧል።
በኢትዮጵያ ያለውን የኢኖቬሽን ስነ-ምህዳር ለማሳደግ እየተሰሩ ያሉ የኢኖቬሽን ስትራቴጂክ ማዕቀፍ እና መሠረተ ልማት እንዲሁም አዳዲስ አሰራሮችን ለዘላቂ ልማት ለመጠቀም የተጀመሩ ስራዎች ለእስራኤል የሉዕካን ቡድን መቅረባቸውን ከኢኖቬሽንና ቴከረኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ መስክ በኢትዮጵያና እስራኤል መካከል ያለውን ፈጠራን እና ትብብር ለማጠናከር እንዲሁም የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ያለመው ይህ ዝግጅት ለአራት ቀናት እንደሚካሄድም ተጠቁሟል፡፡