ለአየር ንብረት ለውጥ የማትበገር አፍሪካን ለመገንባት አህጉራዊ አንድነታችን ወሳኝ ነው- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

You are currently viewing ለአየር ንብረት ለውጥ የማትበገር አፍሪካን ለመገንባት አህጉራዊ አንድነታችን ወሳኝ ነው- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

AMN- ሚያዝያ 01/2018 ዓ.ም

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ ዛሬ በሰው ልጅ መገኛዋ ኢትዮጵያ፣ በአፍሪካውያን መሰባሰቢያ አዲስ አበባ፣16ኛውን የአፍሪካ የሥጋት መከላከል ዐቅም ጉባኤ (ARC-COP16) በይፋ አስጀምረናል ብለዋል።

አህጉራችን በአየር ንብረት ለውጥ ክፉኛ እየተፈተነች ትገኛለች ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ ሆኖም ይህ ፈተና ተስፋችንን የሚያጨልም፣ ጉዟችንን የሚገታ አይሆንም ሲሉ ገልጸዋል።

በእልህ፣ በቁጭትና በእንችላለን ኅብረት አንድነታችንን የምናጠናክርበት አጋጣሚ ነው ሲሉ ነው የጠቀሱት።

እኛ አፍሪካውያን ከአደጋ በኋላ ለሚመጣ ርዳታ እጅ ከመዘርጋት ይልቅ፣ አደጋን ቀድሞ መከላከልና በሳይንሳዊ መንገድ ለመፍትሔ መዘጋጀት የህልውናችን መሠረት ሊሆን ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ራዕይ ሰንቃ፣ ክንዷን አበርትታ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ዐቅም እየገነባች መሆኗን ነው አቶ ተመስገን የገለጹት፡፡

በአረንጓዴ ዐሻራ የምድርን ገጽታ እየቀየርን ነው ፣ በምግብ ሉዓላዊነት ንቅናቄ ራሳችንን ለመቻል እየተጋን ነው ፣ በታዳሽ ኃይል ልማትም የአህጉራዊ ትሥሥር ገመድ እየሆንን ነው ሲሉ አብራርተዋል።

ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች በበዙበት፣ በአንጻሩ ዓለም አቀፋዊ ድጋፎች በቀነሱበት በዚህ ወቅት፣ የአፍሪካ ሥጋትን የመከላከል ዐቅም (African Risk Capacity-ARC) የመሰሉ አህጉራዊ ተቋሞቻችንን ማጠናከር አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ፣ የአደጋ ሥጋትን በጥናት መለየት፣ ቀድሞ መከላከል፣ ችግር ሲከሠትም በአፍሪካዊ ዐቅም ምላሽ መስጠት ይገባል ያሉ ሲሆን ፣ ኢትዮጵያም ለዚህ የአፍሪካውያን ሌላኛው የሉዓላዊነት ግብ መሳካት በአርአያነት እንምትተጋ ገልጸዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review