AMN-ሚያዝያ 05/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ሲነሳ ስማቸው ቀድሞ ከሚጠቀሱት አንጋፋ አሰልጣኞች መካከል ሰውነት ቢሻው ግንባር ቀደም ናቸው።
ብሔራዊ ቡድኑን ከ31 ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የመሩትና የኢትዮጵያውያንን የደስታ ጥም የቆረጡት እኚህ ታላቅ ሰው፣ከሜዳው ድል ጀርባ ያለውንና ለብዙዎች እንግዳ የሆነውን አስገራሚ የሕይወት ውጣ ውረድ ከባለቤታቸው ወይዘሮ እየሩሳሌም ከተማ ጋር አሳልፈውታል።
ጥንዶቹ በአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ የትንሳኤ በዓል ላይ ከአርባ አመታት በላይ የዘለቀውን የትዳር ህይወታቸውን “በኢቫንጋዲ” የመዝናኛ ፕሮግራም አጋርተዋል።
የዛሬው የስኬትና የክብር ማማ ላይ ከመድረሳቸው በፊት ያለፉበት የሕይወት ፈተና የሚጀምረው የመምህርነት ስራቸውን ትተው በባህር ዳር ከተማ የቀበሌ ሊቀመንበር ሆው ተመርጠው በሚያገለግሉበት ወቅት ነበር።
በወቅቱ ጋሽ ሰውነት ሕግን ለማስከበርና ድሆችን ለመርዳት ባደረጉት ጥረት፣ በተለይም 42 አቅመ ደካሞችን በነፃ እንዲኖሩ በማድረጋቸውና አንድ ግለሰብ የመንግስትን ቤት እንዲያስረክብ በማስገደዳቸው ምክንያት ከፍተኛ ቂም ተያዘባቸው።

ከህግና አሰር ውጭ ቤቱን የያዘው ግለሰብ በኋላ ላይ ሥልጣን ሲይዝ በፈጠረው የሐሰት ውንጀላ ጋሽ ሰውነት ወደ እስር ቤት እንዲወሰዱ ተደረገ።
በዚያም ከፍተኛ ድብደባና ስቃይ ቢደርስባቸውም፣ በምርመራ ነፃ መውጣት መቻላቸውን ያስረዳሉ።
ሆኖም ግን “ነፃ አብዮታዊ እርምጃ ይወሰድበታል” የሚለው የመንደሩ ሹክሹክታ ሕይወታቸውን በስጋት ላይ ጥሎት ስለነበር፣ ወዳጆቻቸው መኖር ከፈለጉ በአስቸኳይ ማግባት እንዳለባቸው መከሯቸው።
ያኔ ነው ጋሽ ሰውነት በፍቅር ግንኙነት ውስጥ ባልነበሩበት ወቅት ለደኅንነታቸው ሲሉ ብቻ ትዳርን ለማሰብ የተገደዱት።
በጓደኛቸው ጥቆማ ከአዲስ አበባ ወደ ባህር ዳር ተመድባ ትሠራ የነበረችውን እየሩሳሌም ከተማን ለማግኘት ለየት ያለ ዘዴ ተጠቀሙ።
“ከአዲስ አበባ ደብዳቤ ይዤልሽ መጥቻለሁ” በማለት ቢሮዋ ድረስ ቢሄዱም የሰጧት ወረቀት ግን ባዶ ነበር። “መልክቱ ያለው እኔ ጋር ሳይሆን አንቺ ጋር ነው፤ እሱም ማግባት እፈልጋለሁ የሚል ነው” በማለት በቀጥታ ጥያቄ ማቅረባቸውን በአግራሞት ያስታውሳሉ።
“በጥያቄ አቀራረቡ ብናደድም በወቅቱ የእኔም እህት ለእስር መዳረጓ፣እሱንም ከመግደል ወደኋላ እንደማይሉ በማመን ከሞት ልታደገው ከቻልኩ ይሁን ብዬ የእንጋባ ጥያቄውን ተቀበልኩ” ሲሉ ባለቤታቸው ወ/ሮ እየሩሳሌም ከተማ ተናግረዋል።
በሦስት ወራት ውስጥ ወደ ትዳር የገቡት ጥንዶቹ፣በባህር ዳር በነበራቸው የመጀመሪያ የትዳር ዓመት ጋሽ ሰውነት ባለቤታቸውን በብስክሌት አፈናጥጠው ከሥራ ወደ ቤት ይመልሷት የነበረው ትዝታ ዛሬም ድረስ በናፍቆት የሚታወስ ነው።
ሆኖም ባለቤታቸው ወደ አዲስ አበባ ስትዛወር ጋሽ ሰውነት ለተጨማሪ አንድ ዓመት ባህር ዳር በመቅረታቸው የደረሰባቸው የናፍቆት ስቃይ እጅግ ከባድ ነበር። “ለአንድ ዓመት ስንለያይ ሰው ሁሉ ነበር ያለቀሰው፤ በጣም ይከብዳል፣ ስራው ላይ ራሱ ትኩረት እንዳታደርግ ያደርግሃል” ይላሉ ጋሽ ሰውነት ያንን የመለያየትና የናፍቆት ጊዜ ሲያስታውሱ።
ወደ አዲስ አበባ ተዛውረው ከመጡ በኋላም ሕይወት አልጋ በአልጋ አልነበረችም፣የራሳቸውን ቤት ለመሥራት ሲነሱ በእጃቸው ላይ በቂ ብር እንኳን ሳይኖራቸው በባንክ ብድርና በጽናት ነበር የተነሱት።
በሁለት መቶ አምሳ ብር መሬት ተረክበው፣ ከባንክ 22 ሺህ ብር ተበድረው የአሁኑን ቤታቸውን መሥራት ቢጀምሩም፣በመሀል ግን ከሥራ መታገድና “የመንግሥቱ ኃይለማርያም ሚስት ወንድም ነው” የሚል የሐሰት ወሬ መሰማቱ ለሁለት ወራት ያህል ከባድ ፈተና ደቀነባቸው።
በህይወት ዘመኔ ሁለት ወር ብቻ ነው ስራ ያልሰራሁት በወቅቱም የባንክ ዕዳ መክፈል ባለመቻላችን ቤቱ እንዳይሸጥም የስድስት ወር የማገገሚያ ጊዜ ለባንክ ከስገባን ጥቂት ቀናት በኋላ ደህና ስራ አገኘሁ ሲሉም ያን የጭንቅ ያስታውሳሉ።
ቁጠባን ባህል ያደረገው የህይወት ጉዟቸው፣ወደ ጀርመን ለትምህርት ማቅናታቸው የፈጠረው ዕድል የ30 ዓመት ብድርን በ13 ዓመታት ውስጥ ከፍለው ቤቱን የግላቸው ለማድረግ አስችሏቸዋል።
ለዚህ ሁሉ ስኬታቸው “75 በመቶ ድርሻ የምትወስደው ባለቤቴ ናት” በማለት ውለታዋን በአድናቆት ይናገራሉ።

ጋሽ ሰውነት በየስፖርት ክለቡና በብሔራዊ ቡድን ሲዞሩ፣ ቤቱንና አራት ልጆቹን ሙሉ በሙሉ ተረክባ ለቁም ነገር ያበቃቻቸው ባለቤታቸው ነበረች።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ አፍሪካ ዋንጫ ማለፉ ሲረጋገጥ በቤታቸው የነበረው ደስታ ወደር አልነበረውም። ልጆቹ በደስታ ጠረጴዛ እስኪገለብጡ ድረስ ፈንጥዘው ሲጨፍሩ፣ ባለቤታቸው ግን ያን ትልቅ ድል ስትሰማ በፍጥነት የሄደችው ወደ ቤተክርስቲያን ነበር።
በፍቅር፣ በመተሳሰብ እና በመከባበር ላይ የተመሰረትው የአሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው 40 አመታትን የዘለቀው የትዳር ጉዞ ለበርካቶች ዓርአያ የሚሆን ነው።
በሚካኤል ኅሩይ