አዲስ አበባ የፕሮጀክት አፈጻጸም ልህቀት ማሳያ ናት- የአፍሪካ ሀገራት የፕሮጀክት ማኔጅመንት ባለሙያዎች

You are currently viewing አዲስ አበባ የፕሮጀክት አፈጻጸም ልህቀት ማሳያ ናት- የአፍሪካ ሀገራት የፕሮጀክት ማኔጅመንት ባለሙያዎች

AMN- ሚያዝያ 6/2018 ዓ.ም

በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት አዘጋጅነት አዲስ አበባ በተካሄደው ዓመታዊ የፕሮጀክት ማኔጅመንት ውይይት ላይ የታደሙ የአፍሪካ ሀገራት ባለሙያዎች፣ በከተማዋ የተከናወኑ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።

ባለሙያዎቹ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ በአዲስ አበባ ከተማ የተመለከቱት የፕሮጀክት አፈጻጸም አስደማሚና ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተሞክሮ የሚሆን ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ጋናዊው ጆርጅ አሶማኒ፣ በከተማዋ የተመለከትኩት የግንባታ ቴክኖሎጂ እና የመሠረተ ልማት ግንባታ፣ አዲስ አበባ ራዕይን ወደ ተግባር የመቀየር ትልቅ ምሳሌ መሆኗን አሳይቶኛል ብለዋል።

ኬንያዊቷ ጂዓኒ ማቴንጌ በበኩሏ፣ ወደ አዲስ አበባ የመጣሁት ለመጀመሪያ ጊዜ ቢሆንም፣ በከተማዋ ውበትና በግንባታ ሥራዎቿ ጥበብ በእጅጉ ተደምሜያለሁ፤ ይህም ለፕሮጀክት አፈጻጸም አርአያ የሚሆን ተግባራዊ ማሳያ ነው ብላለች፡፡

ከሦስት ዓመት በፊት የነበረችውን አዲስ አበባ አሁን ላይ ለማስታወስ እንደሚያዳግት የገለጸው ደግሞ ማላዊው ኮንዲዋኒ ምታሊማንጃ ሲሆን፣ አዲስ አበባ ከተማ ፈጣን የልማት ለውጥ ታይቶባታል ብሏል።

ይህ ሊሆን የቻለው ደግሞ በፈጣን የፕሮጀክት አፈጻጸም ምክንያት መሆኑን አንስቷል።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ታምራት ሙሉ እንደገለጹት፣ አዲስ አበባ ፕሮጀክቶችን በላቀ ደረጃና ፍጥነት እንድትፈጽም ያስቻሏት፣ ፕሮጀክቶቹ ከውስጥ በተገኘ ሀብት መከናወናቸው እና በሥራዎቹ ላይ ሕዝቡን በንቃት ማሳተፍ በመቻሉ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በጥቂት ዓመታት ውስጥ የተመዘገበው ይህ ፈጣን የልማት ጉዞ፣ በአሁኑ ወቅት ለብዙ የአፍሪካ ሀገራት እንደተሞክሮ እየቀረበ ይገኛል ብለዋል።

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review