ታሪካዊዉ እና ተጠናክሮ የቀጠለዉ የኢትዮጵያ እና የላይቤሪያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት

You are currently viewing ታሪካዊዉ እና ተጠናክሮ የቀጠለዉ የኢትዮጵያ እና የላይቤሪያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት

AMN ሚያዝያ 6/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ እና የላይቤሪያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን እ.አ.አ 1958 የተጀመረ ሲሆን በቅኝ አገዛዝ ዘመን የአፍሪካ ድምፅ በመሆን የነበራቸው ሚና የላቀ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

የዛሬው የአፍሪካ ኅብረት መሰረት የሆነውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በመመስረት ረገድ ግንባር ቀደም የነበሩት ኢትዮጵያና ላይቤሪያ ዛሬም ታሪካዊ ወዳጅነታቸውን በተለያዩ ዘርፎች አጠናክረዉ ቀጥለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በላይቤሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት ያበረከተችው የሰላም ማስከበር ድጋፍ ለዛሬው ወዳጅነት ወሳኝ ምዕራፍ እንደሆነ ይነገራል።

በተለይም እ.አ.አ. ከ2003 ጀምሮ በተባበሩት መንግስታት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ስር የተሰማራው የኢትዮጵያ ሰራዊት ላይቤሪያን ወደ ሰላም ለመመለስ፣ ታጣቂዎችን ትጥቅ በማስፈታት፣ ምርጫዎችን በሰላም እንዲጠናቀቁ በመጠበቅ እና ለንጹሃን ዜጎች ሰብአዊና የህክምና እርዳታ በማድረስ ረገድ መስዋዕትነት ከፍሏል።

የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ያሳየው ከፍተኛ ዲሲፕሊን እና ለላይቤሪያውያን የነበረው ቅርበት ዛሬም ድረስ በአገሪቱ የሰላም አየር እንዲነፍስ ትልቅ አሻራ ጥሏል።

እ.አ.አ በ2020 የተቋረጠው እና ወደ ላይቤሪያ ዋና ከተማ ሞንሮቪያ የሚደረገው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ከኅዳር 20 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በድጋሚ መጀመሩ ደግሞ በሁለቱ አገራት መካከል የንግድና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን አጠናክሯል።

ለውጡን ተከትሎ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚዊ ዘርፍ እያሳየች ያለውን ፈጣን እድገት፤ ላይቤሪያ በግብርና፣ በመሠረተ ልማት እና በጤና ዘርፎች ያሉ የልማት ተሞክሮዎችን ለመቅሰም ፍላጎቷን በተደጋጋሚ ገልጻለች።

ትናንት አመሻሽ የላይቤሪያ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ንዩማ ቦአካይ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ከልዑካን ቡድናቸው ጋር የዲፕሎማሲ ማዕከል ወደሆነችው መዲናችን አዲስ አበባ መግባታቸው የሁለቱን አገራት ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግር ይጠበቃል።

ፕሬዝዳንቱ በቆይታቸው በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ይጎበኛሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቆይታቸው ፍሬያማ ውይይት እንደሚኖራቸው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የላይቤሪያ ፕሬዝደንት ጆሴፍ ንዩማ ቦአካይ ከ39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ጎን ለጎን አካሂደዉ በነበረዉ የሁለትዮሽ ውይይት በቴክኖሎጂ በተለይም ኢትዮጵያ ለመመስረት ባቀደችው በዓለም 2ኛ በአፍሪካ ደግሞ 1ኛ በሆነው የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ ዙሪያ መምከራቸው ይታወሳል።

በትዝታ መንግስቱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review