AMN ሚያዝያ 2/2018
የኢየሱስ ክርስቶስን ስቅለት ስናስብ እርስ በርሳችን ይቅርታ በማድረግና ፍጹም ፍቅር በመስጠት ሊሆን ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሀነ ኢየሱስ ሱራፌል ገለጹ።
የስቅለት በዓል በልደታ ማሪያም ካቶሊክ ካቴድራል ቤተክርስቲያን በርካታ ምዕመናን በተገኙበት በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቶች ታስቧል።
ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል በዚሁ ወቅት፣ የስቅለት በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ ድኅነት ሲል የደረሰበትን ግርፋት፣ ስቃይ፣ መከራና በመስቀል ላይ መቸንከሩን የምናስታውስበት ነው ብለዋል።
ኢየሱስ ክርስቶስ በስቅለቱና በሞቱ የሰውን ልጅ አድኗል ያሉት ብፁዕ ካርዲናሉ፥ በመስቀሉ ላይ ሆኖ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ብሎ ይቅርታን ማስተማሩንም አስረድተዋል።
ዕለቱ እኛም የበደሉንን ይቅር ብለን፣ ለእርቅና በሰላም የምንጸልይበት ቀን ነው ብለዋል።

ምዕመኑ በዚህ ቀን በፆም፣ በጸሎት፣ በስግደት እና ንስሐ በመግባት ከጌታው ጋር እርቅ የሚያወርድበት መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ሁላችንም በሰራነው ሀጢያት በማዘንና ፈጣሪን ይቅርታ በመለመን፣ እርስ በርስ በመተሳሰብ፣ በመፋቀርና የተጎዱትን በማሰብ በዓሉን ማክበር ይገባል በማለትም መልዕክታቸውን ማስተላለፋቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።