በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ባለ3 ወለል ዘመናዊ የመኖሪያ ህንፃ ለሀገር ባለውለታዎችና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ተላለፈ

You are currently viewing በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ባለ3 ወለል ዘመናዊ የመኖሪያ ህንፃ ለሀገር ባለውለታዎችና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ተላለፈ

AMN ሚያዝያ 3/2018 ዓ.ም

የቤት ግንባታውን ክፍለ ከተማው ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ጋር በመተባበር አስገንብቶታል፡፡

በዚህ ቤት የማስተላለፍ መርሀ-ግብር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ ወይዘሮ ቡዜና አልቃድር ፣ የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈፃሚ ምስክር ነጋሽ (ዶ/ር) ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ቅድስት ወልደ ገብርኤል፣ የአዲስ አበባ ከተማ ኢኖቤሽን ቢሮ ሀላፊ አቶ አወሉ ሙሀመድ የክፍለ ከተማው የዲሞክራሲ ስርአት ግባንታ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ ብርሀኑ አበራና በየደረጃው ያሉ ሀላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ቡዜና አልቃድር ባስተላለፉት ሰፊ መልዕክት ተለዋዋጭ በሆነው ዓለማዊ ሁኔታ የሰዎች አኗኗር ለማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ተጋላጭ መሆኑን ገልጸው በተለይም በዓለማችን አንዱ ክፍል የሚፈጠር ችግር በሌላው ላይ ተፅዕኖ በሚያሳርፍበት በዚህ ወቅት ታዳጊ ሀገራት ፈታኝ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

እነዚህን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት እና ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ዋነኛው በር ከፋች የሆነውን ድህነትን ማሸነፍ እንደሚገባ የጠቆሙት አፈ ጉባኤዋ ለዚህም የከተማዋን አማራጮች መጠቀምና አቅሞችን ወደ ሀብት መቀየር የግድ መሆኑን ተናግረዋል።

የለውጡ መንግስት የቤትና መንገድ ልማት፣ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማቶችን እያከናወነ እንደሚገኝና ከዚሁ ጎን ለጎንም ባለሀብቶች በሪል እስቴት፣ በሆቴልና በማምረቻ ዘርፎች ከተማዋን ውብ ከማድረግ ባለፈ ለነዋሪው ሰፊ የስራ እድል እየፈጠሩ መሆኑን ገልጸዋል። በዛሬው ዕለትም በከተማ ደረጃ 208 ቤቶች ለሀገር ባለውለታዎች የተላለፉ ሲሆን የቂርቆስ ክፍለ ከተማም ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ጋር በመተባበር የገነባውን ውብ ህንፃ መርቆ ማስረከቡን አብስረዋል።

የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ምስክር ነጋሽ በበኩላቸው መንግስት ለሰው ልጆች ካለው ቅን አመለካከት በመነሳት አቃፊና ደጋፊ ለሌላቸው የሀገር ባለውለታዎች ሰፊ የሰው ተኮር ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በከተማዋ እየተሰሩ ያሉ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ልማት ስራዎች የኢትዮጵያውያንንና የአፍሪካውያንን ብቻ ሳይሆን የዓለም መንግስታትንና ህዝቦችን ቀልብ የሳቡ መሆናቸውን ያስረዱት ዋና ስራ አስፈፃሚው በዛሬው ዕለት ቀደም ሲል በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ወገኖችን ችግር የፈታ ግንባታ መጠናቀቁን ይፋ አድርገዋል።

እንደ ዶክተር ምስክር ገለጻ ቀደም ሲል ግለሰቦቹ ይኖሩበት የነበረው ስፍራ በክረምትና በንፋስ ወቅት እጅግ የሚፈታተንና ቤት ተብሎ ለመጥራት የሚያዳግት የነበረ ቢሆንም አሁን ግን በሃያ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር ወጪ ባለ ሶስት ወለል (G+3) ህንፃ ተገንብቶለታል። ለዚህም ግንባታ ሃያ ሶስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብሩ በኢኖቬሽን ቢሮ ሲሸፈን ቀሪው ደግሞ በክፍለ ከተማው የተሸፈነ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚሁ መርሃ ግብር ላይ በግንባታው ምክንያት ተነስተው የነበሩ 12 ነዋሪዎች ግንባታው ሲጠናቀቅ ባሉበት ወደ ቤታቸው እንዲገቡ የማድረግና በ 25 ነዋሪዎች ህጋዊ መኖርያ ቤት ያልነበራቸው ለአመታት በሰው ቤት ተጠግተው ይኖሩ በመሆናቸው ከተማ አስተዳደሩ የቤት ስጦ የቤት እድለኛ አባወራዎችና እማወራዎች የቁልፍ ርክክብ ስነ-ስርአት አብሮ የተከናወነ ሲሆን ይህም የበዓል ወቅት ላይ መከናወኑ ደግሞ ደስታውን እጥፍ እንደሚያደርገው ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ቅድስት ወልደ ገብርኤል በበኩላቸው ይህ የቤት ማስተላለፍ መርሃ-ግብር ላይ ቁልፍ የሚረከቡ 25 ነዋሪዎች ህጋዊ መኖርያ ቤት ያልነበራቸው በልማት ቤት ሲፈርስ ለአመታት በሰው ቤት ተጠግተው ይኖሩ የነበሩ ምንም ቤት ያልነበራቸው በመሆናቸው ከተማ አስተዳደሩ የቤት ስጦታ በማበርከት መብት የፈጠረላቸው ናቸው ብለዋል።

ከተማ አስተዳደራችን “ሰው ተኮር” ለሆኑ የማህበራዊ አገልግሎት ስራዎች የሰጠውን ልዩ ትኩረት በተግባር ያሳየ ነውም ያሉት ኃላፊዋ የቤት እድለኛ ተጠቃሚዎቹ አርፈውና ተረጋግተው የሚኖሩበት የራሳቸው ሰነድ ያለው መኖሪያ ቤት ባለቤት እንዲሆኑ አስተዳደሩ አድርጓል ብለዋል፡፡

ወይዘሮ ቡዜና አልቃድር በመልዕክታቸው ማጠቃለያ ላይ ገንዘባቸውን፣ ጉልበታቸውንና እውቀታቸውን ላበረከቱ በጎፈቃደኞች ምስጋናቸውን አቅርበው የከተማው አስተዳደር እንዲህ አይነት በጎ ስራዎች ባህል ሆነው እንዲቀጥሉ በትጋት እንደሚሰራና የገቡትን ቃል በተግባር እያረጋገጡ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ዶክተር ምስክር ነጋሽም በበኩላቸው ግንባታው መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንዲሁም የበጎፈቃደኛ አመራሮች ተሳትፎ የታየበት መሆኑን ገልጸው ለመላው የዕድሉ ተጠቃሚዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። ዘገባዉ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ነዉ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review