ታሪካዊ የተባለለት የአሜሪካ እና ኢራን ድርድር በፓኪስታን ተጀመረ

You are currently viewing ታሪካዊ የተባለለት የአሜሪካ እና ኢራን ድርድር በፓኪስታን ተጀመረ

AMN – ሚያዝያ 3/2018 ዓ.ም

በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ከግማሽ ምዕተ ዓመት ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ የከፍተኛ ደረጃ ድርድር በፓኪስታን ተጀምሯል።

ሁለቱ ሀገራት እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ለማቆም ውይይት እያደረጉ ቢሆንም፣ የሀገራቱ ግንኙነት ግን አሁንም በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ይገኛል።

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራንን 28 የማዕድን ማጓጓዣ መርከቦች እንዳወደሙ እና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሲባል የሆርሙዝ የባህር ሰርጥን የማጽዳት ሥራ መጀመራቸውን በትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል።

ኢራን በበኩሏ ይህንን መረጃ “ሐሰተኛ” በማለት አስተባብላለች።

የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት በፓኪስታን ተገናኝተው የሁለት ሰዓታት ውይይት አድርገዋል።

የኢራን ልዑካን ቡድን ለጠቅላይ መሪው አያቶላህ አሊ ካማኒ እና ለሌሎች በስድስት ሳምንታት ጦርነት ለተገደሉ ሰዎች ሀዘናቸውን ለመግለጽ በጥቁር ልብስ ታጅበው ቀርበዋል።

ቴህራን በውጭ ባንኮች የታገዱ ንብረቶቿ እንዲለቀቁ፣ የሆርሙዝ ሰርጥ ቁጥጥር እንዲሰጣት፣ የጦርነት ካሳ እንዲከፈላት እና ሊባኖስን ጨምሮ በቀጣናው የተኩስ አቁም እንዲደረግ ፍላጎቷን ገልፃለች።

አሜሪካ በበኩሏ፣ የባህር ሰርጡ ለዓለም አቀፍ መርከቦች ነጻ እንዲሆን እና ኢራን አቶሚክ ቦንብ ማምረት እንደማትችል ለማረጋገጥም የኒውክሌር ማበልጸግ መርሐ ግብሯን እንድትተው ትሻለች።

እስከ አሁን በሁለቱ ወገኖች መካከል የተደረገ ስምምነት መኖሩ ባይገለፅም፣ በተለይም የኢራን የታገዱ ንብረቶች መለቀቅን በተመለከተ አሜሪካ የቀረበውን ሀሳብ ውድቅ ማድረጓን ሮይተርስ ዘግቧል።

በዓለም ላይ ያለውን የነዳጅ ዋጋ በእጅጉ ያናረው ይህ ጦርነት፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወትም ቀጥፏል።

በፓኪስታን የተጀመረው ይህ ድርድር ጦርነቱን በማቆም ረገድ ምን ለውጥ ያመጣል የሚለው በጉጉት እየተጠበቀ ነው።

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review