AMN ሚያዝያ 4/2018
በአሜሪካ እና ኢራን መካከል በኢስላማባድ ሲካሄድ የነበረዉ ድርድር ያለ ስምምነት መጠናቀቁ ተገለጸ።
የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ በኢስላማባድ በተካሄደው ከፍተኛ የሰላም ንግግር አሜሪካ እና ኢራን ስምምነት ላይ አለመድረሳቸውን ገልጸዋል።
ቫንስ ፈቃደኛ ሆነዉ ወደ ንግግሩ ቢመጡም በኑክሌር ማልማት ምክንያት ድርድሩ ያለ ዉጤት ሊጠናቀቅ መቻሉን ተናግረዋል።
ኢራን የኑክሌር መሣሪያዎችን ላለማልማት ቁርጠኝነቷን ማሳየት ይኖርባታል ብለዋል ምክትል ፕሬዝዳንቱ።
ጄዲ ቫንስ ከንግግሩ በኋላ ከልዑኮቻቸዉ ጋር ፓኪስታንን ለቀው መዉጣታቸዉ ተገልጿል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ በፖኪስታን ሰፋ ያለ ዉይይት መደረጉን ገልጾ፣ ዋሽንግተን ተገቢ ያልሆኑ ጥያቄዎችን ከማቅረብ እንድትቆጠብ አሳስቧል።
ንግግሩ ሊካሄድ የቻለው የሁለቱም ልዑካን ቡድን አባላት የመደራደር ስልጣን ስለነበራቸው እንደሆነም የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጨምሮ ገልጿል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከፖኪስታን ንግግር ቀደም ብለዉ በሰጡት አስተያየት በስምምነት ላይ መደረስ አለመደረሱ ለእሳቸው ምንም ልዩነት እንደማያመጣ እና ምንም ቢፈጠር እኛ እናሸንፋለን ማለታቸዉን ቢቢሲ ዘግቧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ሁለት የባህር ኃይል አውዳሚ መርከቦች የባህር ላይ ፈንጂዎችን የማጽዳት ስራ መጀመራቸዉን አስታዉቋል።
መርከቦች በሆርሙዝ የባህር ሰርጥ በኩል ማለፋቸውም ተገልጿል።
ነገር ግን ኢራን ይህንን አባባል አስተባብላለች።
እስራኤል በሄዝቦላህ ኢላማዎች ላይ ጥቃቷን ስትቀጥል፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ በበኩላቸዉ ከሊባኖስ ጋር ዘላቂነት ያለው የሰላም ስምምነት ማድረግ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
በወንድማገኝ አሰፋ