AMN ሚያዝያ 14/2018
ኢትዮጵያን ወደሚመጥናት ብልፅግናና ከፍታ ለማድረስ መገናኛ ብዙሃን የድህረ እውነት ዘመን የሚጠይቀውን አስተዋይነትና ስክነት መላበስ እንዳለባቸው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራልና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የቦርድ ሰብሳቢ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለጹ።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ባለፉት ሶስት ወራት በክልል የሕዝብ እና የማህበረሰብ መገናኛ ብዙኃን ላይ ያደረገውን የይዘት ስርጭት ክትትልና ግምገማ ውጤት ይፋ ማድረጊያ መርሃ ግብር አዘጋጅቷል።
መገናኛ ብዙኃን ለሀገር ግንባታና ለማህበረሰብ አመለካከት ቀረፃ በሚል መሪ ሃሳብ በሚካሄደው መርሐ ግብር ላይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቴ አለነ፣ የክልል የሕዝብ መገናኛ ብዙሃን የሥራ ኃላፊዎች እና የማህበረሰብ የመገናኛ ብዙኃን ተወካዮች ተገኝተዋል።
አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ዓላማ በዝሃነት ማጉላት፣ የማህበረሰቡን ተስፋ ማሳየትና ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ ሚናቸውን መወጣት ነው።

ለኢትዮጵያ ጠንካራ የሀገረ መንግስት ግንባት ብዝሃነትን አጉልቶ በማሳየት የማህበረሰቡን ቋንቋ፣ ባህልና እሴት ማሳደግ ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ብዝሃ ማንነትና ቀለም እንዳላት መረዳት እንደሚገባም ገልጸዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያን ወደ ሚመጥናት ብልፅግናና ከፍታ ለማድረስ መገናኛ ብዙሃን የድህረ እውነት ዘመን የሚጠይቀውን አስተዋይነትና ስክነት መላበስ አለባቸው ብለዋል።
የድህረ እውነት ዘመን ሃሰት፣ ለቅሶና ሟርት ገበያውን የሚቆጣጠርበት ዘመን መሆኑን ጠቅሰው፣ መገናኛ ብዙሃን ይሄንን ታሳቢ ባደረገ አስተውሎት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ኢትዮጵያዊነት እንዲያብብ የሚያደርግ ሥራ ከሁሉም የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት እንደሚጠበቅ ገልጸው፤ ጉድለቶች እንዲታረሙ እውነት እንዲወጣ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማቱን የክህሎትና የሀብት ውስንነቶችን ለመሙላት በጋራ መስራትና ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ መግለጻቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡