AMN ሚያዝያ 27/2018 ዓ.ም
በርካታ የዓለም ሃገራት፤ ሃገራቸዉን እና ወገናቸዉን በታማኝነት ያገለገሉና ታሪክ የሰሩ የሃገር ባለዉለታዎችን በተለያዩ መንገዶች ይዘክሯቸዋል፡፡
ከእነዚህ መካከል የሃገር ባለዉለታዎችን ታሪክ በፅሁፍና በሰነድ በማቆየት እንዲታሰቡ ማድረግ አንዱ ሲሆን የባለዉለታዎቹን የትግል፣ የድል እና የሥራ ጉዞ የሚዘክሩ መጽሐፍት ተፅፈው ለትውልድ እንዲቀመጡ ይደረጋል፡፡
የሃገር ባለዉለታዎች የሚታቡበት ሌላኛዉ መንገድ ዘጋቢ ፊልሞችን መስራት ሲሆን በህይወት ያሉትን ምስክርነቶች በመቅዳትና የታሪክ ሰነዶችን በማሰባሰብ ለዕይታ እንዲበቃ በማድረግ ባለዉለታዎች ይዘከራሉ፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ ሃገራት የሃገር ባለዉለታዎችን ስም ከቋሚ ቅርሶች ጋር በማያያዝ እንዲታሰቡ ያደርጋሉ፡፡ አደባባዮችን፣ መንገዶችን፣ ትምህርት ቤቶችን፤ ሆስፒታሎችን ሕንጻዎችንና ሌሎችን በስማቸው በመታሰቢያነት በመሰየም ያስቧቸዋል፡፡

ሐውልት ማቆም ሌላኛዉ የሃገር ባለዉለታዎች መታሰቢያ ሲሆን በሰሩት ስራ ልክ በታዋቂ ስፍራዎች ላይ ሐውልት በማቆም ለትውልድ አርአያ እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡
የሃገር ባለዉለታዎችን ለዕውቀትና ለጥናት ማዕከልነት መጠቀም ሌላኛዉ መታሰቢያ ሲሆን በምርምር ተቋማትና በቤተ-መጻህፍት፤ በፈጠራ ዘርፍ ስማቸውን የሚዘክር የትምህርት ዕድል ፈንድ በማቋቋም ወጣቶች እንዲበረታቱ ይደረጋል፡፡
በሃገር ባለዉለታዎች ስም በዓላትንና ክብረ-በዓላትን ማዘጋጀት ሌላኛዉ መታሰቢያ ሲሆን የተወለዱበትን ወይም ያረፉበትን ቀን በማሰብ ስለ ስራዎቻቸው ሲምፖዚየሞችና ውይይቶች እንዲዘጋጁ ይደረጋል፡፡
በሃገር ባለዉለታዎች ስም የሽልማት መርሃ-ግብሮች የሚዘጋጁ ሲሆን በባለዉለታው ስም የሚሰየሙና ለተተኪ ሰራተኞች የሚሰጡ የላቀ ውጤት ሽልማቶች እንዲዘጋጁ ይደረጋል፡፡

ትልቁና ዋነኛው የመታሰቢያ አላማ ባለዉለታዎቹ ለሃገር የሰሩትን መልካም ስራ እንደ አርአያ በመውሰድ፣ ያቆዩትን ሃገርና ህዝብ በታማኝነት ማገልገልና የጀመሩትን የልማት ወይም የነፃነት ጉዞ ዳር ማድረስ ነው።
ባለዉለታዎችን ማሰብ ማለት ያለፈውን ታሪክ ማድነቅ ብቻ ሳይሆን፣ ለወደፊቱ ትውልድ ጠንካራ መሠረት መጣልም ጭምር ነው።
እርስዎስ የሃገር ባለዉለታዎችን እንዴትና በምን ያስባሉ? ሃሳብዎን ያጋሩን
በወንድማገኝ አሰፋ