AMN – ግንቦት 13/2018 ዓ.ም
ሁለት በታሪክና በጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ የሚራራቁ፣ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በፈጣን የከተማ ገጽታ ግንባታና በዘመናዊነት ሽግግር ተመሳሳይ ታሪክ እየጻፉ ያሉ ከተሞች።
የካስፒያን ባህር ዕንቁ የሆነችው የአዘርባጃኗ መዲና ባኩ እና የአፍሪካና የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችው አዲስ አበባ።
ባኩ ከድሮው የሶቪየት ዘመን ታሪክ ወጥታ በዘመናዊ አርክቴክቸርና በፅዱ የከተማ እቅድ የዓለምን ትኩረት መሳብ የቻለች፣ አዲስ አበባ ደግሞ በታላላቅ የኮሪደር ልማትና የሜጋ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ራሷን በከፍተኛ ፍጥነት እያደሰች ያለችበት ወርቃማ ወቅት ላይ የምትገኝ ከተማ ናት።
ይህ የሁለቱ መዲናዎች የለውጥ ጉዞ፣ አንዷ ከአንዷ የሚማማሩበት ሰፊ የልማትና የፖሊሲ ተሞክሮ ይዟል። የከተማን “ያለፈ የደበዘዘ ” ገጽታ ወደ “ብሩህ” እና አረንጓዴነት የመቀየር ጥበብ

ባኩ በአንድ ወቅት በነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካዎች፣ በጭስና በኢንዱስትሪ ቆሻሻ ተበክላ “ጥቁር ከተማ” (Black City) ትባል የነበረውን ሰፊ ቀጠና፣ አስደናቂ በሆነ የአካባቢ ጥበቃና የምህንድስና ጥበብ ወደ ዘመናዊው “ባኩ ብሩህ ከተማ” (Baku White City) መቀየር ችላለች።
ይህ ታላቅ ተሞክሮ፣ አዲስ አበባ አሮጌ፣ ለአገልግሎት አስቸጋሪና ለብክለት የተጋለጡ የከተማዋን ክፍሎች በማፍረስ፣ በምትካቸው ለዜጎች ክብር የሚመጥን መኖሪያ ቤቶች፣ለአይን የሚማርኩ አረንጓዴ ፓርኮችን፣ የብስክሌት መንገዶችንና ዘመናዊ መንደሮችን ለምታስገነባበት የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ፍጹም ማሳያና ትልቅ የስኬት ማረጋገጫ ነው።
ታሪካዊ ቅርሶችን ከ”ስማርት ሲቲ” (Smart City) ፅንሰ-ሃሳብ ጋር የማስማማት ሚስጥር
ባኩ የዩኔስኮ የዓለም ቅርስ የሆነውን የድሮውን ታሪካዊ ከተማ ክፍል (Icherisheher) ጥንታዊ ማንነት ሳታናጋ ጠብቃ ማቆየት የቻለችው፣ አዳዲሶቹንና ሰማይ ጠቀስ ህንፃዎቿን ለብቻቸው ለይቶ በታቀደ ስልት በመገንባት ነው።
አዲስ አበባም እንደ ፒያሳና አካባቢው ያሉ ታሪካዊና የቅርስ ይዘት ያላቸውን ስፍራዎች ማንነት ሳይበረዝ፣ ለቱሪስት ሳቢ በሆነ መልኩ የማደስና የከተማዋን ጥንታዊ ታሪክ ከዘመናዊው የዲጂታልና ዘመናዊ ከተማ ግንባታ ጋር የማዋሃድ ጥበብን ከባኩ ሰፊ ልምድ መቅሰም ትችላለች።

የባህር ዳርቻ ልማት (Baku Boulevard) እና የአዲስ አበባ ወንዞች ተፋሰስ የባኩ ከተማ ዋነኛ መለያና የቱሪስት መሳቢያ የሆነው፣ በካስፒያን ባህር ዳርቻ ላይ በኪሎ ሜትሮች ርዝመት የተዘረጋው የ”ባኩ ቡሌቫርድ” (Baku Boulevard) መናፈሻ፣ ለከተማዋ ነዋሪዎች ሰፊ የመዝናኛ፣ የስፖርትና የባህል ማዕከል ሆኖ ያገለግላል።
ይህ ስኬት፣ አዲስ አበባ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ በጀትና ጥራት እየገነባች ላለችው፣ የከተማዋን ወንዞችና ተፋሰሶች ወደ ውብ መዝናኛ ስፍራነት እየቀየረች ላለችው ”የወንዞች ዳርቻ ልማት” ፕሮጀክት ዘላቂ የአሰራር ልምድ ትልቅ ግብዓት የሚሆን ነው።
የዲጂታል ሽግግር እና የዘመናዊ ትራንስፖርት (E-Mobility) ውህደት፤ ባኩ በቴክኖሎጂ የታገዘ የትራፊክ ቁጥጥር፣ የህዝብ ትራንስፖርት ትስስር እና የዲጂታል ከተማ አስተዳደርን (E-Government) በከፍተኛ ደረጃ ተግባራዊ አድርጋለች።
አዲስ አበባም “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030” ስትራቴጂን ይዛ ወደፊት እየተገሰገሰች ባለችበትና የአረንጓዴ ትራንስፖርት (የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን) በስፋት እያስተዋወቀች እና እየተገበረች ባለችበት በዚህ ወቅት፣ የትራፊክ መጨናነቅን በቴክኖሎጂ ለመቀነስና የከተማ አገልግሎቶችን ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝ ለማድረግ በመሶብ አንድ ማዕከል የተጀመሩ እና እየተስፋፉ ያሉ ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ከባኩ ዘመናዊ አሰራር ብዙ ልምድ ትቀስማለች ።
ዓለም አቀፍ ሁነቶች (MICE Tourism) እና የከተማ ብራንዲንግ ፤ ባኩ እንደ ፎርሙላ 1 (Formula 1) ውድድር፣ የዩሮቪዥን የሙዚቃ ፌስቲቫል እና የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ጉባኤ (COP29) ያሉ ታላላቅ ዓለም አቀፍ ኩነቶችን በስኬት በማስተናገድ ከተማዋን የዓለም የቱሪስት መዳረሻና የምርት ስም (Brand) አድርጋታለች።

የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባም፣ አዳዲሶቹን እንደ አድዋ ድል መታሰቢያ ያሉ ታላላቅ ታሪካዊ መናፈሻዎችና የስብሰባ ማዕከላትን በመጠቀም፣ ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽኖችን፣ የስፖርት ውድድሮችንና ዲፕሎማሲያዊ ጉባኤዎችን በስፋት በመሳብ የቱሪዝም ገቢዋን ማሳደግ ትችላለች ይህንን መንገድም ጀምራዋለች።
አዲስ አበባም ለባኩ የምታካፍለውና የምታስተምረው ትልቅ አገራዊ እሴት አላት። ይህም በአጭር ጊዜ ውስጥ ታላላቅና ውስብስብ ፕሮጀክቶችን ሌሊትና ቀን በቁርጠኝነት 24/7 በመስራት የምታሳይበት አስደናቂ የ”አዲስ አበባ ፍጥነት” (Addis Ababa Speed) ነው።
በተጨማሪም፣ የመንግስት፣ የህዝብና የግል ባለሀብቱን አቅም በበጎ ፈቃደኝነትና በአንድነት በማስተባበር ረገድ ያላት ልምድ ለባኩም ቢሆን አዲስ የልማት ስልት ሊሆናት ይችላል።
ማህበራዊ ደህንነትና ቀደምት የህፃናት ልማት (ECD) ስኬት አዲስ አበባ በከተማ ደረጃ ተግባራዊ ያደረገችውና በአሁኑ ወቅት በርካታ አገራት እንደ ምሳሌ እየወሰዱት ያለው የ”ቀዳማይ ልጅነት ልማት ” (Early Childhood Development – ECD) መርሃ-ግብር፣ በከተማዋ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ማህበረሰቦች ለመደገፍ የተዘረጉት የምገባ ማዕከላትና የተማሪዎች ድጋፍ ፕሮጀክቶች ትልቅ ማህበራዊ ስኬቶች ናቸው።

ከተማን ማዘመን ብቻ ሳይሆን ሰውንም ማልማት መሆኑን የምታሳይበት ይህ የአዲስ አበባ ልምድ፣ ባኩ ማህበራዊ ፍትሃዊነትን ይበልጥ ለማረጋገጥ በፖሊሲ ደረጃ ልትወስደው የምትችለው ትልቅ ትምህርት ነው።
የወደፊት “የእህትማማች ከተሞች” ትስስር በመጨረሻም፣ ባኩ እና አዲስ አበባ የባህል፣ የታሪክና የኢኮኖሚ ትስስራቸውን በማጠናከር “የእህትማማች ከተሞች” (Sister Cities) ስምምነታቸውን ይበልጥ ማጎልበት ይኖርባቸዋል።
የሁለቱ ታላላቅ ከተሞች እርስ በእርስ መማማርና በልማት ልምድ መለዋወጥ፣ በማደግ ላይ ያሉ ከተሞች የራሳቸውን ታሪካዊ ማንነት ሳይለቁ እንዴት ወደ ዘመናዊነት፣ ብልጽግና እና ሁሉን አቀፍ ልማት መሻገር እንደሚችሉ ለቀሪው ዓለም የሚያሳይ ህያው ምስክር ይሆናል።
በያለው ጌታነህ