የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለሀገር ዕድገት ያላቸው ሁለንተናዊ ጠቀሜታ

You are currently viewing የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለሀገር ዕድገት ያላቸው ሁለንተናዊ ጠቀሜታ

AMN- ግንቦት 13/2018 ዓ.ም

በአሁኑ ወቅት በርካታ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት የኢኮኖሚ መዋቅራቸውን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

ይህንን ሽግግር ለማፋጠን ደግሞ መሰረተ-ልማት የተሟላላቸው ልዩ የኢኮኖሚ ቀጠናዎች የሆኑት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባር ቀደም መፍትሄ ሆነው ብቅ ብለዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለሀገር ዕድገትና ለዜጎች ሕይወት መሻሻል ቁልፍ ጠቀሜታዎች መካከል በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዜጎች፣ በተለይም ለወጣቶችና ለሴቶች ቀጥተኛ ስራዎችን ይፈጥራሉ።

ከዚህ ባለፈ በትራንስፖርት፣ በምግብ አቅርቦትና በአገልግሎት ዘርፎች በርካታ ቀጥተኛ ያልሆኑ የስራ ዕድሎችን በማስገኘት የዜጎችን ገቢ ያሳድጋሉ።

ሀገራት ጥሬ ዕቃ ብቻ ከመላክ ወጥተው እሴት የተጨመረባቸውን አልባሳት፣ የቆዳ ውጤቶችና የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን ወደ ውጭ በመላክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እንዲያገኙ ያስችላል።

በሌላ በኩል ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ በመተካት የሀገርን ወጪ ይቀንሳሉ። መብራት፣ ውሃ፣ መንገድ እና የቴሌኮም መሠረተ-ልማትን በአንድ ማዕከል ስለሚያቀርቡ፣ ታዋቂ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶችን በቀላሉ ለመሳብ ዋነኛ መሣሪያ ናቸው።

ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ይዘዋቸው የሚገቡት ዘመናዊ ማሽነሪዎችና የአመራረት ጥበባት ለአገር ውስጥ ባለሙያዎችና መሃንዲሶች ከፍተኛ የክህሎት ሽግግር በመፍጠር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ያደርጋቸዋል።

ፓርኮች በሚገነቡባቸው አካባቢዎች አዳዲስ መንገዶች፣ የሕክምናና የትምህርት ተቋማት አብረው ይስፋፋሉ። በተጨማሪም ዘመናዊ የቆሻሻ ማጣሪያ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የኢንዱስትሪ ተረፈ-ምርቶች አካባቢን እንዳይበክሉ በስርዓት ለመቆጣጠር ይመቻሉ።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች የፋብሪካዎች ስብስብ ብቻ ሳይሆኑ፤ የሀገርን የኢኮኖሚ መዋቅር የሚቀይሩ፣ የዜጎችን ሕይወት የሚያሻሽሉ እና ሀገርን በዓለም አቀፍ የንግድ መድረክ ላይ ተወዳዳሪ የሚያደርጉ የዕድገት ሞተሮች ናቸው።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review