AMN- ግንቦት 14/2018 ዓ.ም
አዲሱ የለሚ ሁለገብ የገበያ ማዕከል ቀደም ሲል በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ የነበሩ ስብራቶችን በመጠገን፣ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሕብረተሰቡ ተደራሽ እንደሚያደርግ የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሀቢባ ሲራጅ አስታወቁ።
ወይዘሮ ሀቢባ ሲራጅ ፣ ምርታማነትንና አቅርቦትን በመጨመር የነዋሪውን የኑሮ ጫና ለማቃለል በከንቲባ አዳነች አቤቤ አቅጣጫ ሰጪነት ሰፊ ሥራዎች መከናወናቸውን አስታውቀዋል።
አገልግሎት እየሰጡ ያሉ አዳዲስ ዘመናዊ የገበያ ማዕከላትም አምራችና ሸማችን በቀጥታ ማገናኘት በመቻላቸው አላስፈላጊ የሆኑ ደላሎችንና የንግድ ሰንሰለቶችን ማሳጠር መቻሉን ኃላፊዋ ገልጸዋል።

ይህም ለከተማው ነዋሪዎች የግብርና እና የኢንዱስትሪ ፍጆታ ምርቶችን በስፋትና በውጤታማነት በማቅረብ ጤናማ የግብይት ሥርዓት ለመፍጠር ትልቅ እገዛ ማድረጉን ነው የጠቀሱት።
የገበያ ማዕከላቱ የነዋሪውን የኑሮ ጫና ለማቃለል ከፍተኛ ትኩረት እንደተሰጠ ማሳያ መሆናቸውን ያነሱት ቢሮ ኃላፊዋ፣ ማዕከላቱ ፍትሐዊ የገበያ ውድድር ላይ የተመሠረተ አገልግሎት እንዲሰጡ አስፈላጊው ክትትልና ድጋፍ በየደረጃው እንደሚደረግም አረጋግጠዋል።

በወርቅነህ አቢዮ