AMN – ግንቦት 17/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ1 ሺህ 447ኛው ለዒድ አለ-አድሃ (ዓረፋ) በዓል የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥን ለመቀነስ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
በተለይም በበዓላት ሰሞን ደንበኞች ቀኑን በድምቀት ለማክበር ከወትሮው የተለየ የኃይል አጠቃቀም ስለሚኖራቸው፤ መሰረተ-ልማቱ ላይ የሚፈጠረውን ከፍተኛ ጫና ለመቀነስ አገልግሎቱ በልዩ ትኩረት የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱንም አስታውሷል፡፡
ከበዓሉ አስቀድሞ ከተሰሩ ስራዎች መካከል የመካከለኛና የዝቅተኛ ማሰራጫ መስመሮችን የመፈተሸ፣ የረገቡ የኤሌክትሪክ ገመዶችን የመወጠር፣ የእንጨት ምሰሶዎችን በኮንክሪት የመቀየር፣ የኃይል ጫና ያለባቸውን ትራንስፎርመሮችን ዓቅም የማሳደግና አዲስ ትራንስፎርመሮችን የመትከል ስራዎች ይገኙበታል፡፡
በዚህም አገልግሎቱ የሚያስተዳድረውን ነባር መሰረተ ልማት ላይ ሙሉ ለሙሉ የቅድመ መከላከል ፍተሻ ማድረጉን የአገልግሎቱ መረጃ ያመላክታል፡፡
ለኃይል መቆራረጥ መንስኤ ከሆኑ ግኝቶች መካከል በዋናው ኔትዎርክ 80 በመቶ እንዲሁም በትራንስፎርመር 70 በመቶ የሚሆኑትን መቅረፍ መቻሉ ተገልጿል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን በዋዜማውና በበዓሉ ዕለት የኃይል መቆራረጥን ለመቀነስ፤ ሲከሰትም አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እንዲሁም አስተማማኝና ቀልጣፋ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማቅረብ በሁሉም የተቋሙ አደረጃጀቶች የአስቸኳይ ጥገና ግብረ-ሃይል መዋቀሩ ተጠቅሷል፡፡
በበዓሉ ዕለት በተመረጡ ማዕከላት የቅድመ ክፍያ የካርድ መሙላት አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን ተጠቃሚ ደንበኞች የገዙትን የኃይል መጠን ማለቅና አለማለቁን በማረጋገጥ በዓሉ ከመድረሱ በፊት አስቀድመው እንዲሞሉ አገልግሎቱ መክሯል፡፡