የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሊታሰብ የማይችል አስደናቂ ሥራ ሠርቷል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN – ግንቦት 19/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት ጥቂት ዓመታት በትምህርት፣ በስፖርት ፣ በጤና፣ በመሠረተ ልማት እና በኢነርጂ ዘርፎች ሊታሰብ የማይችል አስደናቂ ሥራ መሥራቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት በምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የጤና ተቋም የሆነው የላፍቶ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ነው።

በወቅቱም ከተማ አስተዳደሩ ላከናወናቸው አስደናቂ ሥራዎች የመላው ኢትዮጵያ እና የአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ እንደሚያመሰግነው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ላለፉት አሥርት ዓመታት ስትከተለው የነበረው የጤና ፖሊሲ ከበሽታ መከላከል ባለፈ ማከም ላይም ትኩረት ባደረገ መልኩ መሻሻሉን አስታውቀዋል፡፡

በሽታን መከላከል በተሟላ ሁኔታ ሊሳካ የሚችለው አካባቢያዊ ችግሮች ሲቀረፉ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የወንዞች መቆሸሽ፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎች አለመኖር እንዲሁም አዛውንቶች በምቾት የሚንቀሳቀሱበትና የሚያርፉበት ስፍራ ማጣት ለጤና ሥርዓቱ ተግዳሮት እንደሚሆኑ ጠቅሰዋል።

ይህንንም ችግር ለመቅረፍ የከተማ አስተዳደሩ የጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

“በሽታ ልክ እንደ ጦር ሠራዊት ውጊያ ይፈልጋል፤ ውጊያ ደግሞ ትጥቅ ይፈልጋል፤ ትጥቁም ምግብ ነው” በማለት በከተማዋ የተገነቡት የምገባ ማዕከላት የማካፈልን ባህል እያሳደጉ መሆናቸውን አብራርተዋል።

በተለይም ተማሪዎች በትምህርት ቤቶች በቀን ሁለት ጊዜ የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ መደረጉ ጤናማ ትውልድን የመገንባት እንደሚያስችል አንስተዋል፡፡

አያይዘውም ኢትዮጵያ ዜጎቿን ሙሉ በሙሉ መመገብና መርዳት እስክትችል ድረስ፣ ዜጎች በትብብር መንፈስ ችግሮችን ማለፍ እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል፡፡

በትዝታ መንግስቱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review