AMN- ግንቦት 20/2018 ዓ.ም
ማንችስተር ሲቲ ምናልባት ማንም ሊደግመው የማይችል ታሪክ የሰራለትን አሰልጣኝ በክብር ሸኝቷል።
10 ዓመት የቆየው የ55 ዓመቱ አሰልጣኝ የክለቡን የዋንጫ መደርደሪያ ሞልቶ ነው የለቀቀው።
በርካታ ዋንጫዎችን ማሸነፍ የቻለው ፔፕ ጋርዲዮላ በማንችስተር ሲቲ ቆይታው ታሪክ ሁሌም የሚዘከሩለት ጀብዱዎችን ፈጽሟል።
በቁጥራዊ መረጃው ይበልጥ የሚታወቀው ኦፕታ የቀድሞ የባርሰሎና እና ባየርን ሙኒክ አሰልጣኝ የሲቲን ቆይታ ሊገልጹ የሚችሉ ቁጥራዊ መረጃዎችን አስፍሯል።
20 ዋንጫዎች ፔፕ ጋርዲዮላ በማንችስተር ሲቲ ቆይታው የትኛውም የክለቡ የቀድሞ አሰልጣኝ አድርጎት የማያውቀው 20 ዋንጫዎችን አንስቷል።
ከእነዚህ ውስጥ ስድስቱ የፕሪምየር ሊግ ድሎች ናቸው። አስልጣኙ በእንግሊዝ በርካታ የሊግ ዋንጫ በማንሳት የሚበለጠው 13 ዋንጫ ባሸነፉት የማንችስተር ዩናይትዱ ታሪካዊው አሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ብቻ ነው።
ፔፕ ለድል ከበቃባቸው ስድስት የሊግ ዋንጫ ውስጥ አራቱ በተከታታይ የተገኙ ናቸው። ይህም በእንግሊዝ የክለብ እግርኳስ ታሪክ አዲስ ሆኖ ተመዝግቧል።

አሰልጣኙ በሲቲ ሁለት የመጨረሻ የውድድር ዓመቱ ፕሪምየር ሊጉን ማሸነፍ አልቻለም ፤ ፔፕ ባርሰሎናን በ2008 ማሰልጠን ከጀመረ በኋላ በሁለት ተከታታይ ዓመት የሊግ ዋንጫ ሳያሸንፍ ሲቀር ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
593 ጨዋታዎችን መምራት ፔፕ ጋርዲዮላ በአስቶንቪላ 2ለ1 የተሸነፈበት የመጨረሻ ጨዋታው በሁሉም ውድድር ሲቲን የመራበት 593ኛ ሆኖ ተመዝግቧል።
ከእነዚህ ጨዋታዎች 416ቱን በድል በማጠናቀቅ የማሸነፍ ንጻሬውን 70.2 በመቶ አድርጓል። ቁጥሩ የክለቡ ቀዳሚው ውጤታማ አሰልጣኝ እንዲሆን አስችሎታል።
ፔፕ ሲቲን በመራባቸው ጨዋታዎች 159 የተለያዩ አሰልጣኞችን የመግጠም ዕድል አግኝቶ 142ቱን ድል አድርጓል።
ፔፕ ከአንድ ጊዜ በላይ ገጥሞ ሊረታቸው ያልቻላቸው አሰልጣኞች ፋቢያን ኸርዝለር ፣ ሮናልድ ኩመን ፣ ብሩኖ ጄኔሲኦ እና አልቫሮ አርቤሎዋ ናቸው።
2.28 በጨዋታ በአማካይ ያስመዘገበው ነጥብ በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ 20 እና ከዚያ በላይ ጨዋታ ከመሩ አሰልጣኞች መካከል በአማካይ በርካታ ነጥብ በማግኘት ፔፕ ጋርዲዮላን የሚስተካከል የለም።

በሊጉ 380 ጨዋታዎችን የመራው ፔፕ 269ኙን ያጠናቀቀው በድል ነው።
በጨዋታ በአማካይ 2.28 ነጥብ አስመዝግቧል። በዚህ ቁጥር በጨዋታ በአማካይ 2.16 ካስመዘገቡት ሰር አሌክስ ፈርጉሰንም በልጦ በመሪነት ደረጃ ላይ አስቀምጦታል።
100 ነጥብ በአንድ የውድድር ዓመት የስፔናዊው አሰልጣኝ የመጀመሪያ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ደማቅ ታሪክ ተጽፎበት ነው የመጣው። በ2017/18 የውድድር ዓመት ያሳካው ይህ ድል አሁንም ድረስ ክብረወሰን የሆነ 100 ነጥብ ተመዝግቦበታል።
በውድድር ዓመቱ ከ38 ጨዋታዎች 32ቱን በማሸነፍ አራት አቻ በመለያየት እና በሁለት ሽንፈት ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ በሊጉ ታሪክ ባለ ሶስት ዲጂት አሃዝ አስመዝግቦ ያጠናቀቀው።
106 ኳሶችን ተጋጣሚ መረብ ላይ በማሳረፍም የተለየ የውድድር ዓመት ማሳረፍ ችሏል።
ፕሪምየር ሊጉ በአዲስ መልክ በ1992 ከተዋቀረ በኋላ የትኛውም ክለብ በአንድ የውድድር ዓመት 106 ግቦችን አላስቆጠረም።
111 ተጫዋቾችን መጠቀም ጋርዲዮላ በማንችስተር ሲቲ ቆይታው 111 ተጫዋቾችን ተጠቅሟል።

ከአሰልጣኙ ጋር አብሮ ሲቲን የተሰናበተው በርናርዶ ሲልቫ 460 ጨዋታዎች ላይ በመሳተፍ የፔፕ ተመራጭ መሆኑን አስመስክሯል።
ከሲልቫ ቀጥሎ ኬቨን ደብሩየና 381 ጨዋታዎችን በማድረግ ይከተላል።
በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ በመግባት ግን ግብ ጠባቂው ኤደርሰንን የሚያክል የለም። ባለፈው ዓመት ሲቲን የለቀቀው ብራዚላዊው ግብ ጠባቂ 371 ጨዋታዎችን በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ተካቶ ተጫውቷል።
ግብ በማስቆጠር ረገድ በንጽጽር ከፔፕ ጋር ያሳለፈው ጊዜ አጭር ቢሆንም 162 ግቦችን በማስመዝገብ ኧርሊንግ ሃላንድ ከሁሉም ልቆ ይገኛል። ሰርጂዮ አጉዌሮ በ124 እንዲሁም ራሂም ስተርሊንግ በ120 ግቦች ይከተላሉ።
ግብ የሆኑ ኳሶችን በማመቻቸት ከኔቨን ደብሩየናን የሚስተካከል አልተገኘም። አሁን ለናፖሊ የሚጫወተው ቤልጄማዊው አማካይ 158 ኳሶችን አመቻችቶ አቀብሏል።
ደብሩየናን የሚከተለው በርናርዶ ሲልቫ ደግሞ 75 ወደ ግብነት የተቀየሩ ኳሶችን ማመቻቸት ችሏል።
በሸዋንግዛው ግርማ