AMN- ግንቦት 27/2018 ዓ.ም
ነገ ግንቦት 28 ቀን 2018 ዓ.ም (የአውሮፓውያኑ ሰኔ 5) “የዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ቀን” በዓለም አቀፍ እና በአህጉር አቀፍ ደረጃ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ይከበራል።
ዕለቱ በተለይ አካባቢን ለሰው ልጆች ምቹ፣ ጤናማ እና ሳቢ ከማድረግ አንጻር የተጀመሩ ታላላቅ ንቅናቄዎችንና የጋራ ኃላፊነቶችን ለመገምገም ታላቅ መድረክ እንደሚሆን ይጠበቃል።
ምድርን ከአየር ንብረት ለውጥ አደጋ ለመታደግ እና የተፈጥሮ ሥነ-ምህዳሩን ወደ ነበረበት ለመመለስ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተያዙ አምስት ዋና ዋና ስትራቴጂካዊ አቅጣጫዎች እና አህጉራዊ እውነታዎች ተጠቃሽ ናቸው።
የመጀመሪያው ከተሞችን ለሰው ልጅ መኖሪያ ምቹ የማድረግ ጉዳይ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ከግማሽ በላይ የሚሆነው የዓለም ህዝብ በከተሞች ውስጥ እንደሚኖር መረጃዎች ያመለክታሉ።
በመሆኑም ከተሞችን ምቹ ለማድረግ ከተለመደው የህንፃ ግንባታ ወጥቶ እንደ ፓርኮች፣ የደኖች ልማት እና የወንዞች ዳርቻ ልማት ያሉ “አረንጓዴ መሠረተ-ልማቶችን” ማስፋፋት ግድ የሚልበት ወቅት ላይ መደረሱ ማሳያ ነው።

እነዚህ ስራዎች የሙቀት ማዕበልን ከመቀነስ ባለፈ የአየር ብክለትን በማሻሻል የሰዎችን አካላዊና አእምሯዊ ጤንነት ለመጠበቅ ያላቸው ሚና የጎላ መሆኑ ነው።
በሌላ በኩል የዓለም ሙቀት መጨመር እና ድንገተኛ የአየር ንብረት መዛባቶችን ለመግታት፤ እንደ የፓሪሱ የአየር ንብረት ስምምነት ያሉ ዓለም አቀፍ መድረኮች አገራት የበካይ ጋዝ ልቀትን እንዲቀንሱና ወደ ታዳሽ ኃይል እንዲሸጋገሩ እያስገደዱ ናቸው።
በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ትኩረቱን “ዜሮ ልቀት” ላይ በማድረግ መጪው ትውልድ ንጹህ አየር የሚተነፍስባት ምድር እንዲረከብ በትጋት እየተሰራ ይገኛል።
ወደ አፍሪካ አህጉር ስንመጣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ከተጀመሩ ግዙፍና አስደናቂ ስራዎች መካከል “የታላቁ አረንጓዴ ግንብ” ንቅናቄ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል።
ይህ ፕሮጀክት ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራትን በአረንጓዴ ተክሎች ሰንሰለት በማገናኘት፣ የአፈር መሸርሸርን ለመግታት፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ያለመ አህጉራዊ ተግባራትም ተጠቃሽ ናቸው።
ከዚህ በተጨማሪ የቆሻሻ አወጋገድ እና የፕላስቲክ ብክለትን ለመዋጋት የመልሶ ጥቅም ላይ ማዋል ኢኮኖሚ በዓለም ዙሪያ ትልቅ ትኩረት አግኝቷል።
የሚጣሉ ቆሻሻዎችን ወደ ሀብት መቀየር፣ የፕላስቲክ ምርቶችን በአፈር ውስጥ በቀላሉ በሚሟሙ ቁሶች መተካት እና ለአካባቢ ጥበቃ ተስማሚ የሆኑ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን ማበረታታት የዘመናችን ቁልፍ መፍትሄዎች ናቸው።
ዓለም አቀፍ ስምምነቶችና አህጉራዊ እቅዶች ብቻቸውን ለውጥ አያመጡም ስለሆነም እውነተኛ ለውጥ የሚጀምረው ከግለሰብ ደረጃ መሆኑን ጥናቶች ያመላክታሉ።
ነገ የሚከበረው የአካባቢ ቀን እያንዳንዳችን በአካባቢያችን ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ፣ የፕላስቲክ አጠቃቀማችንን በመቀነስ፣ እና አረንጓዴ ስነ-ምህዳርን ባህል በማድረግ ለሰው ልጅ የምትመች ውብ ዓለምን ለመፍጠር የድርሻን መወጣት ከሁሉም ይጠበቃል።
በያለው ጌታነህ