ቦርዱ መራጩ ህዝብ ስለ ፓርቲዎች በቂ ግንዛቤ ኖሮት ድምጽ የሚሰጥበትን እድል ማመቻቸቱን አስታወቀ

AMN- ግንቦት 21/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ መራጩ ህዝብ ስለ ፓርቲዎች በቂ ግንዛቤ ኖሮት ድምጽ የሚሰጥበትን እድል ማመቻቸቱን አስታውቋል፡፡

ቦርዱ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚፎካከሩ ፓርቲዎች ፖሊሲዎቻቸውን የሚያስተዋውቁበትን እና አንዳቸው ከሌላቸው የሚለዩበትን ወይም የሚመሳሰሉበትን ፕሮግራምና ዓላማ በግልጽ ለህዝብ የሚያሳውቁበትን አጋጣሚም ፈጥሯል፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሃይሉ እንዳሉት፤ ምርጫ ቦርድ መራጩ ህዝብ ስለ ፓርቲዎች በቂ ግንዛቤ ኖሮት ድምጽ የሚሰጥበትን እድል አመቻችቷል፡፡

ተደራሽነትን ለማስፋት በአምስት ቋንቋዎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር ለህብረተሰቡ መተላለፉን ሰብሳቢዋ ያስታወቁ ሲሆን የማህበራዊ ሚዲያን ጨምሮ በሁሉም አማራጮች ለህብረተሰቡ ተደራሽ ተደርጓል ብለዋል፡፡

በዋና የፖሊሲ ጥናት ምሁራን ፣ የጥናት ባለሙያዎች በመታገዝ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ፕሮግራም በማስጠናትና ፓርቲዎችም ፍላጎታቸው የሚለካበት መረጃ በመሰብሰብ ሥራዎች ሲሰሩ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡

ውጤታማነቱን ለመመዘን መጠይቅ ከተሰጣቸው ውስጥ 70 በመቶ የሚሆኑት መራጮች ግንዛቤ እንዳገኙ እና ክርክሩም መራጮች ድምፅ እንዲሰጡ እንዳነሳሳቸው ተጠቁሟል፡፡

የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሃይሉ ፤ በእስካሁኑ ሂደት ለውጤታማነቱ የተጉ ባለሙያዎችን፣ የፓለቲካ ፓርቲዎችን ፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶችን እና በስልጠናና ሰነድ በማደራጀት የተሳተፉ አካላትን አመስግነው ምርጫው በተሳካ መልኩ እንዲካሄድ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የሻምበል ምህረት

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review