የዓለም ሀገራት ምርጫን ለምን ያካሂዳሉ ?

AMN- ግንቦት 21/2018 ዓ.ም

ምርጫ በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ የሕዝብን የሥልጣን ባለቤትነት የሚያረጋግጥ ዋና መሣሪያ ነው።

ምርጫ ለአንድ ሀገር የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ዕድገት በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡

ከነዚህ መካከል፡-

1. የሕዝብ ውክልናን ማረጋገጥ

ምርጫ ዜጎች ፍላጎታቸውን፣ እምነታቸውንና ጥቅማቸውን የሚያስጠብቁላቸውን መሪዎችና ተወካዮች በነፃነት እንዲመርጡ ዕድል ይሰጣል። በዚህም የተመረጡ አካላት የሕዝብ እውነተኛ ተወካይ ሆነው እንዲሠሩ ያደርጋል።

2. ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር መፍጠር

ሥልጣንን በኃይል ወይም በግርግር ከመያዝ ይልቅ፣ በሕዝብ ድምፅና በሰላማዊ መንገድ ከአንድ መሪ ወይም ፓርቲ ወደ ሌላው ለማስተላለፍ ምርጫ ብቸኛውና አስተማማኙ መንገድ ነው።

ይህ ለአገር መረጋጋትና ዘላቂ ሰላም ወሳኝ ነው።

3. ተጠያቂነትን እና ግልጽነትን ማስፈን

የተመረጡ መሪዎች ለሰጡት ተስፋና ለሚያከናውኑት ሥራ ለሕዝብ ተጠያቂ እንዲሆኑ ያደርጋል።

ሕዝብን በታማኝነት ካላገለገሉ በሚቀጥለው ምርጫ በድምፅ ሊወርዱ እንደሚችሉ ስለሚያውቁ፣ ሥራቸውን በኃላፊነትና በግልጽነት ለማከናወን ይገደዳሉ።

4. ሕጋዊነትን መስጠት

በነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ሥልጣን የያዘ መንግሥት በሕዝብ ዘንድም ሆነ በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ዘንድ ሙሉ ተቀባይነትና ሕጋዊነት ይኖረዋል።

ይህም መንግሥት ያወጣቸውን ፖሊሲዎችና ሕጎች ሕዝቡ በፈቃደኝነት እንዲቀበልና እንዲተገብር ያግዛል።

5. የዜጎችን ቀጥተኛ ተሳትፎ ማሳደግ

ምርጫ ዜጎች በአገራቸው የወደፊት ዕድልና ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ላይ በቀጥታ እንዲሳተፉ ያደርጋል።

ድምፅ በመስጠት ሂደት ውስጥ መሳተፍ የዜግነት ክብርንና ኃላፊነትን ያሳድጋል።

6. የፖሊሲና የአማራጭ ሐሳቦች ፉክክር

የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አገርን የሚጠቅሙ አማራጭ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የፖለቲካ ፖሊሲዎችን ይዘው እንዲቀርቡ ያደርጋል።

ይህ የሐሳብ ፉክክር ሃገር የተሻለ የዕድገት አቅጣጫ እንድትመርጥ ይረዳታል።

ምርጫ የሕዝብ ድምፅ የሚሰማበት፣ የመንግሥት ሥልጣን የሚወሰነዉ በሕዝብ ድምጽ መሆኑ የሚረጋገጥበትና የሕግ የበላይነት የሚሰፍንበት የዴሞክራሲ ምሰሶ ነው።

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review