የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ በመምሰል የሿሿ ወንጀልና የሞባይል ስርቆት የፈጸሙ 7 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

AMN- ሰኔ 2/2018 ዓ.ም

የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ በመምሰል የሿሿ ወንጀልና የሞባይል ስርቆት የፈጸሙ 7 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

ፖሊስ እንደገለጸው፤ ተጠርጣሪዎቹ የወንጀል ድርጊቱን የፈጸሙት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ልዩ ቦታው ሳሪስ አቦ የትራፊክ መብራት አካባቢ ነው።

ተጠርጣሪዎቹ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3 A 02122 ኦሮ በሆነ ሚኒባስ ተሽከርካሪ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪና ተጠቃሚ በመምሰል አዲሱ መኮንንና ኢሳያስ ደገፋ የተባሉ የግል ተበዳዮችን በመጫን ጥቂት እንደተጓዙ ኪሳቸው ውስጥ የነበረውን የሞባይል ስልክ እና ገንዘብ ለመውሰድ ሲሞክሩ የግል ተበዳዮች ወንጀሉን ለመከላከል በሚሞክሩበት ወቅት ገፍትረዋቸው በፍጥነት በመጓዝ ላይ ሳሉ ከሌላ ተሽከርካሪ ጋር በመጋጨት ቆመዋል።

በወቅቱ ድርጊቱን በተመለከተው የአካባቢው ህብረተሰብና በትራፊክ ፖሊስ አማካኝነት በተሽከርካሪው ውስጥ የነበሩ ትዕግስት ጌታቸው፣ ገነት ደሳለኝ፣ ሜላት ጌታቸው፣ እየሩሳሌም ጌታነህና መአዛ ማሞ የተባሉ ተጠርጣሪዎችን ከ6 የተለያዩ ስማርት ሞባይል ስልኮችና 11 ሚሞሪ ካርዶች ጋር ሊያዙ መቻላቸውን ተገልጿል፡፡

እንዲሁም በተጠርጣሪዎች ላይ ተገቢው ምርመራ የማስፋት ተግባር እየተከናወነ ሲሆን ሌሎች ያልተያዙ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋልም ከፍተኛ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ፖሊስ ገልጿል።

በተያያዘም በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ልዩ ቦታው ቡልቡላ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ፖሊስ ከህብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ የሞባይል ስርቆት ወንጀሉ ይፈጽማሉ የተባሉ ሀብታሙ ዮሃንስ እና አንተነህ ዮሃንስን በቁጥጥር ስር በማዋል ባደረገው ምርመራ 4 ስማርት የሞባይል ስልኮችን ይዟል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች እየተንቀሳቀሱ ወንጀሉን የሚፈፅሙ በመሆናቸው በእነዚህ ተጠርጣሪዎች ወንጀል የተፈጸመባቸው አዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በመቅረብ ስልኮቻቸውን መረከብ እንደሚችሉ ፖሊስ አስታውቋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review