የአዲስ አበባ የዲጂታል ጉዞ ተሞክሮን ወደ ክልል ከተሞች ለማዳረስ እየተሠራ ነው

AMN – ሰኔ 04/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ አገልግሎቶቿን ዘመኑን የዋጁ ለማድረግ በምታደርገው የዲጂታል ጉዞ ያስመዘገበቻቸውን ውጤት ተሞክሮዎች ወደ ሌሎች የክልል ከተሞች ለማዳረስ እየተሠራ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ።

ሚኒስትሩ ይህንን የገለጹት የፌደራልና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት፣ የአዲስ አበባ የሲቪል ምዝገባና የነዋሪዎች አገልግሎት ኤጀንሲ መረጃ በዘመናዊ መንገድ ለማደራጀት እያከናወነ ያለውን ተግባር ለመመልከት በተደረገ የጉብኝት መርሐ-ግብር ላይ ነው።

በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፣ በዲጂታል 2025 ስትራቴጂ በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውን አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የታዩ ጅምሮችን የማጠናከርና ጉድለቶችን የመሙላት ሥራዎች በዲጂታል 2030 ስትራቴጂ አማካኝነት በስፋት እየተከናወኑ ይገኛሉ።

አያይዘውም የወረቀት ሰነዶችን ወደ ዲጂታል ሥርዓት መቀየር አሁን ላይ የሕይወት ጉዳይ መሆኑን በማንሳት፣ የበርካታ ወሳኝ ሰነዶች መገኛ በሆነው በአዲስ አበባ የሲቪል ምዝገባና የነዋሪዎች አገልግሎት ኤጀንሲ ውስጥ ይህ የሪፎርም ሥራ በስፋት እየተተገበረ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮሴፍ ንጉሴ በበኩላቸው፣ ቀደም ሲል መረጃዎች በወረቀት መቀመጣቸው ለአያያዝ አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ ለተለያዩ ሕገ-ወጥ ተግባራት ያጋልጥ እንደነበርና ዜጎችንም ለከፍተኛ እንግልት ይዳርግ እንደነበር አስታውሰዋል።

በመሆኑም ነባር የወረቀት መረጃዎችን ወደ ዲጂታል ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ማስገባቱ መሰል ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ ሚናው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ የዲጂታል ሥርዓት ነዋሪው ባለበት ሆኖ የሚፈልገውን አገልግሎት በተሳለጠ መንገድ የሚያገኝበትን ሰፊ ዕድል እንደሚፈጥር የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ አዲሱ አሠራር በቅርቡ በይፋ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምርም አረጋግጠዋል።

በመቅደስ ደምስ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review