AMN ሰኔ 6/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለስፖርቱ ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረትና ባከናወናቸው ግዙፍ የስፓርት መሠረተ ልማት ግንባታዎች ምክንያት መዲናዋ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድድሮች በስፋት የሚስተናገዱባት ቀዳሚ ተመራጭ የስፖርት ማዕከል መሆን ችላለች።
ባለፉት ዓመታት በከተማዋ የተገነቡት ከ1 ሺህ 580 በላይ የሕዝብና የወጣቶች ስፖርት ማዕከላት ማኅበረሰባዊ ተሳትፎን ከማሳደግ ባለፈ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማስተናገድ ትልቅ መሠረት ተጥሏል።

በቅርቡ በታላቅ ድምቀት የተጠናቀቀውና በመስቀል አደባባይ የተካሄደው 19ኛው የኢትዮጵያ ግማሽ ማራቶንን ጨምሮ ከተማዋ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የብስክሌት፣ የአትሌቲክስ፣ የጎዳና ላይ ሩጫና ሌሎች የስፖርት ሁነቶችን በስኬት በማስተናገድ መዲናዋ ምቹ ፥ እና ተመሪጭ ከተማ መሆንዋን በተግባር እያሳየች ትገኛለች።

አዲስ አበባ አሁን ላይ የስፖርት ልሂቃን መገናኛ የትላልቅ ውድድሮችና የደጋፊዎች ድምቀት የምታስተናግድ ደኅንነቷ የተጠበቀና ውብ መዲና ሆናለች።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በከተማ አስተዳደራችን የተከናወኑት የተቀናጁ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች፣ የወንዝ ዳርቻዎች እና ደረጃቸውን የጠበቁ የስፖርት ማዕከላት መስፋፋት የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ለስፖርት ቱሪዝም ዕድገት ትልቅ አቅም ፈጥረዋል።

ይህ የስፖርት ቱሪዝም ዕድገት ከስፖርታዊ ፋይዳው ባሻገር፣ ለሆቴል ኢንዱስትሪው፣ ለትራንስፖርት ዘርፉና ለአካባቢው አነስተኛና ጥቃቅን የንግድ አንቀሳቃሾች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መነቃቃትን ፈጥሯል።
ይህም የከተማ አስተዳደሩ የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማሳደግ የያዘውን ግብ በከፍተኛ ደረጃ እየደገፈው እንደሚገኝ የከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡