AMN – ሰኔ 14/2018 ዓ.ም

በኢትዮጵያ የተካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሀገሪቱ የዴሞክራሲ ጉዞ ውስጥ ትልቅ ታሪካዊ ምዕራፍ መሆኑን የአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ ሰላምና ጸጥታ ኮሚሽነር ባንኮሌ አዴኦዬ አስታወቁ።
ኮሚሽነሩ ይህን ያሉት የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤት ማሳወቂያ መርሐ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሀመድ አሊ ዩሱፍን በመወከል ንግግር ያደረጉት ኮሽነር ባንኮሌ አዴኦዬ፣ ህብረቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና የኢትዮጵያ መንግስት ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ላደረጉት ስኬታማ እርምጃ ያለውን ልባዊ አድናቆት ገልጿል ብለዋል።
ህብረቱ አባል ሀገራትን በገለልተኝነት፣ በፍፁም ፍትሃዊነት እና ነፃ በሆነ መንገድ የመደገፍ ስልጣኑን ተጠቅሞ ሂደቱን ሲከታተል መቆየቱንም አብራርተዋል።

ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም የተካሄደውን ይህንን ምርጫ ለመታዘብ፣ በቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የሚመራ እና ከ60 በላይ ወጣትና ሁሉን አቀፍ አባላትን ያቀፈ የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን በኢትዮጵያ ተሰማርቶ እንደነበር አስታውሰዋል።
የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን በሂደት የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ አጠቃላይ ገፅታ እና ዝርዝር ግምገማ የያዘ የመጨረሻ ሪፖርት ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግም በንግግራቸው ተጠቁሟል።
የአፍሪካ ህብረት ለኢትዮጵያ ሰላማዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባታ፣ ለሴቶችና ወጣቶች እኩል ተሳትፎ እንዲሁም ለህዝቦች ነፃ ፍላጎት መከበር ያለውን የማይናወጥ ቁርጠኝነት ማረጋገጡንም ኮሚሽነር ባንኮሌ ገልፀዋል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በአህጉሪቱ ያሉ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሰላማዊ፣ ሁሉን አቀፍ እና ሙሉ ተሳትፎ የሰፈነበት ዴሞክራሲን ለማስፈን በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ ያቀረቡት ኮሚሽነሩ፣ ለአፍሪካ አህጉር ዘላቂ ልማት፣ ሰላም እና መረጋጋት ከዴሞክራሲ ውጭ ሌላ አማራጭ የሌለ መሆኑንም በጥብቅ አስገንዝበዋል።
በአስማረ መኮንን