AMN- ሰኔ 16/2018 ዓ.ም
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተና የኢትዮጵያን አሸናፊነት ያበሰረ መሆኑ ተገለጸ።
ምርጫውን አስመልክቶ ከኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ ያደረጉት በፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ በላይ ወዲሻ፣ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት መጠናቀቁ በሀገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ መክፈቱን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ አሸንፋለች የሚባለው አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ከፍተኛ ድምፅ ወይም አብላጫ ድምፅ አግኝቶ መንግሥት ስለመሰረተ ብቻ አይደለም ያሉት አቶ በላይ ወዲሻ፣ ትርጉሙ ከአንድ ፓርቲ ማሸነፍ በላይ ነው ብለዋል።
የድምር ውጤቱ መገለጫዎች የህዝብ የስልጣን ባለቤትነትን የሚያረጋግጥ ነው፡፡
ከአሁን ቀደም በተካሄዱት ሃገራዊ ምርጫዎች የመራጮች ተሳትፎ 35 ሚሊየን አካባቢ የነበረ ሲሆን፣ በዚህ ምርጫ ግን ቁጥሩ ወደ 54 ሚሊየን ከፍ ብሏል ያሉት በፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ በላይ ወዲሻ፣ ይህ የሚያሳየው ህዝቡ በምርጫው ሂደት ላይ ያለው እምነትና ተሳትፎ እየተጠናከረ መምጣቱን የሚያረጋግጥ ነው።
በጠቅላላ ምርጫው የተወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር መጨመሩ: ፖሊሲያቸውንና ስትራቴጂያቸውን ያለምንም ገደብ በነጻነት ለህዝብ ማቅረብ መቻላቸውም ትልቅ ስኬት መሆኑን አቶ በላይ አብራርተዋል፡፡
ምርጫው ፍትሃዊ፣ ዲሞክራሲያዊ፣ አሳታፊ እና ተአማኒ በሆነ መልኩ መካሄዱ በራሱ የሀገሪቱን አጠቃላይ አሸናፊነት ያረጋገጠ ክስተት መሆኑን ነው አቶ በላይ ያነሱት።
ምርጫው ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እስከተካሄደ ድረስ፣ አብላጫ ድምጽ ያላገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የግል ተወዳዳሪዎች የህዝብን ድምጽ ሊያከብሩ ይገባል።
የማሸነፊያ ድምጽ ያላገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከአሸናፊው የፖለቲካ ፓርቲ ጋር አብረው በመሥራት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታን ማጠናከር እንደሚኖርባቸውም አስገንዝበዋል።
የቅድመ ምርጫው ሂደት ግልጽና ዴሞክራሲያዊ መሆኑን የአፍሪካ ህብረት፣ የአውሮፓ ህብረት: የኢጋድ ታዛቢዎችና ሌሎች ታዛቢዎች በሪፖርታቸው መግለጻቸውን ያነሱት ኃላፊው፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድም ምርጫው ያለምንም ጣልቃገብነት መካሄዱን መግለጹን ተናግረዋል።
ይህም የሀገሪቱን ዲሞክራሲያዊ ምህዳር ወደ ላቀ ደረጃ አሸጋግሮታል።
በምርጫ መሸነፍ ተስፋ የሚያስቆርጥ አይደለም ያሉት ኃላፊው፣ ለብዙሃኑ ድምጽ ተገዢ መሆን የሰለጠነ የፖለቲካ አውድ ለመፍጠር እንደሚያግዝም አብራርተዋል።
ድምጽ ያላገኙ የፖለቲካ ፖርቲዎች ከአሸናፊው ፖርቲ ጋር አብረው መሥራታቸው የ21ኛውን ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ የሚመጥንና ሊጠናከር የሚገባው በጎ ባህል መሆኑን ተናግረዋል።
ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በብዛት ወደ ፓርላማ መግባታቸው ሀገራዊ አቅምንና ጉልበትን የሚፈጥር መሆኑንም አቶ በላይ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።
በያለው ጌታነህ