AMN-ሰኔ 17/2018 ዓ.ም

23ኛው የዓለም ዋንጫ ወደ ሀገራቸው የሚሸኙ እና በውድድሩ የሚቆዩ ብሔራዊ ቡድኖችን እየለየ ይገኛል። ዛሬ የምድብ የመጨረሻ ጨዋታዎች ሲጀምሩ ስድስት ግጥሚያዎች ይጠበቃሉ።
ምድብ አንድ
ደቡብ አፍሪካ ከ ደቡብ ኮሪያ ፤ ቼክ ሪፐብሊክ ከ ሜክሲኮ በዚህ ምድብ የሚጠበቁ ጨዋታዎች ናቸው። የመጀመሪያ ሁለት የምድብ ጨዋታዎቿን ያሸነፈችው ሜክሲኮ ቀጣዩን ዙር መቀላቀሏን አረጋግጣለች።
ደቡብ ኮሪያ ፣ ቼክ ሪፐብሊክ እና ደቡብ አፍሪካ ዕጣ ፈንታቸውን ዛሬ ይለያሉ። ኮሪያ ሶስት ነጥብ ስትይዝ ፣ ቼክ እና ደቡብ አፍሪካ አንድ አንድ ነጥብ አላቸው።
ሁለቱም ጨዋታዎች ለሊት 10፡00 የሚጀምሩ ይሆናል።
ምድብ ሁለት

የጣምራ አዘጋጇ ካናዳ ፣ ስዊዘርላንድ ፣ ኳታር እና ቦስኒያ ሄርዞጎቪና በተደለደሉበት በዚህ ምድብ ፤ ስዊዘርላንድ ከ ካናዳ ፣ ቦስኒያ ከ ኳታር ምሽት 4፡00 ይጫወታሉ።
ካናዳ እና ስዊዘርላንድ በተመሳሳይ አራት ነጥብ በመያዛቸው አቻ መውጣት ተያይዘው ወደ ቀጣዩ ዙር እንዲያልፉ ያደርጋቸዋል።
አንድ አንድ ነጥብ ያላቸው ቦስኒያ እና ኳታር በውድድሩ የሚያቆያቸውን ማስተማመኛ ለማግኘት የግድ አንዳቸው ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል።
ምድብ ሶስት

በዚህ ምድብ ሞሮኮ ከሃይቲ በአትላንታ ስታዲየም እንዲሁም ስኮትላንድ ከ ብራዚል በሚያሚ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል። ሁለቱም ጨዋታዎች በተመሳሳይ ለሊት 7፡00 ይጀምራሉ።
ሞሮኮ እና ብራዚል እያንዳንዳቸው አራት ነጥብ ሲይዙ ፣ ስኮትላንድ ደግሞ ሶስት ነጥብ ይዛለች። ከውድድሩ ውጪ መሆኗን ያረጋገጠችው ሃይቲ ምንም ነጥብ የላትም።
በሸዋንግዛው ግርማ
S