AMN- ሰኔ 18/2018 ዓ.ም
በቬንዙዌላ በተከታታይ በተከሰቱ ሁለት ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋዎች ቢያንስ 32 ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ፣ ከ700 በላይ የሚሆኑት የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ በካራካስ ደግሞ ህንጻዎች መውደማቸው ተገልጿል።
ይህንን አስከፊ ክስተት ይፋ ያደረጉት የሀገሪቱ ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ዴልሲ ሮድሪጌዝ ናቸው።
የአሜሪካ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ (USGS) ከአደጋው ቀደም ብሎ ባስቀመጠው ስሌት መሰረት፣ የሟቾች ቁጥር ከ10 ሺህ በላይ የመሆን እድሉ 44 በመቶ እንደሚሆን አሳይቶ ነበር።
የሟቾች ቁጥር ከ100 ሺህ በላይ የመሆን እድሉ ደግሞ 30 በመቶ እንደሚደርስ ነበር የተገመተው።

ይሁንና የተከሰተውን አደጋ ተከትሎ እስከ አሁን የ32 ሰዎች ሕይወት ማለፉ፣ ከ700 በላይ የሚሆኑ ሰዎች እንደቆሰሉና በዋና ከተማዋ ካራካስ ህንፃዎች መፈራረሳቸው ታውቋል፡፡
በመዲናዋ የሚገኙ የነፍስ አድን ሰራተኞች፣ በተደረመሱ ህንጻዎች ፍርስራሽ ስር የተረፉ ሰዎችን ለማውጣት እየተረባረቡ ነው።
አደጋውን ተከትሎ በከተማዋ የሚገኙ ህንፃዎች ሙሉ በሙሉ የኤሌክትሪክ ኃይል ያጡ ሲሆን፣ የሜትሮ ባቡር አገልግሎትም ሙሉ በሙሉ መቋረጡን ቢቢሲ ዘግቧል።
አደጋው የተከሰተው ከዋና ከተማዋ በስተምዕራብ በሚገኝ አካባቢ ሲሆን፣ ርዕደ መሬቱም በሬክተር ስኬል 7.2 እና 7.5 የተለካ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ንዝረቱም እስከ ጎረቤት ሀገር ኮሎምቢያ ዋና ከተማ ቦጎታ ድረስ መሰማቱ ተመላክቷል።
በታምራት ቢሻው