AMN ሐምሌ 16/2018 ዓ.ም

የቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌየር የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን ጎብኝተዋል።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና የቶኒ ብሌየር ኢንስቲትዩት ከፍተኛ አመራሮች በጋራ መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል።

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) ፣ የቶኒ ብሌየር ኢንስቲትዩት የኢትዮጵያን የዲጂታላይዜሽን ጉዞ ለመደገፍ እያደረገ ላለው አበርክቶ ምስጋና አቅርበዋል።
በቀጣይም በሀገራችን የኤአይ ቴክኖሎጂ ልማትን እና ተግባራዊነትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በትብብር መስራታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቅሰዋል፡፡

የቶኒ ብሌየር ኢንስቲትዩት መስራች፣ ሊቀመንበር እና የቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ቶኒ ብሌየር፣ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን እያዘመነ ስለመሆኑ በመናገር ተቋማቸው ከኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር በትብብር ለመስራት ያለውን ሙሉ ቁርጠኝነት ገልጸዋል።

ሁለቱ ተቋማት በኢትዮጵያ ያለውን የኤ.አይ ቴክኖሎጂ ልማት እና ተግባራዊነት ለማረጋገጥ ቀጣይነት ባለው መልኩ በጋራ እንደሚሰሩ መገለጹን ከኢንስቲትዩቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።