ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እያደረገች ያለዉ ድርድር ወደ ወሳኝ ምዕራፍ ተሸጋግሯል

You are currently viewing ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እያደረገች ያለዉ ድርድር ወደ ወሳኝ ምዕራፍ ተሸጋግሯል

AMN ሕዳር 1/ 2019 ዓ.ም

ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት (WTO) አባል ለመሆን የምታደርገው ድርድር ወደ ወሳኝ ምዕራፍ መሸጋገሩ ተገለጸ።

የዓለም ንግድ ድርጅት 8ኛውን የሥራ ቡድን ስብሰባዉን በጄኔቫ፣ ስዊዘርላንድ እያካሄደ ይገኛል።

በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር እና የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ሂደቱ ዋና ተደራዳሪ ወ/ሮ ያስሚን ወሀብረቢ የተመራው የልዑካን ቡድን በስብሰባዉ እየተሳተፈ ይገኛል።

ሚኒስትሯ በመክፈቻ ንግግራቸው እንዳስገነዘቡት፣ የድርጅቱ አባልነት ኢትዮጵያ እያካሄደችው ያለው የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር አካል ሲሆን፣ የቅድሚያ ትኩረት ከተሰጣቸው ተግባራት አንዱ ነው።

ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል መሆኗ የፖሊሲ ቀጣይነትን እና ግልጸኝነትን ከማጠናከሩም በላይ፣ ምርትና ምርታማነትን፣ የውጭ ንግድን እና ኢንቨስትመንትን በማስፋት የሥራ ዕድልን ለመፍጠር አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው።

ከባለብዙ ወገን ስብሰባው ጎን ለጎን፣ የሁለትዮሽ የገበያ ዕድል ድርድር ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ተካሂዷል።

ከሁለቱም ወገኖች ጋር የተካሄደው ድርድር እጅግ ፍሬያማ እንደነበር የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

እስካሁን ለሁለትዮሽ ድርድር የጠየቁ 17 ሀገራት ሲሆኑ፣ ከ11 ሀገራት ጋር ስምምነት ተፈርሟል።

የድርድር ቡድኑ ቀሪ ባለብዙ ወገን የእንጥልጥል ጉዳዮችን በውይይት ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን ሚኒስትሯ አረጋግጠዋል።

ሚኒስትር ያስሚን ወሀብረቢ በማጠቃለያ ንግግራቸው፣ የተገኘውን ፍጥነት ለመጠበቅ እና ድርድሮችን በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ወደ ተሳካ መደምደሚያ ለማድረስ ቀጣይነት ያለው ቁርጠኝነት፣ የጋራ ኃላፊነት እና በሁሉም ባለድርሻ አካላት መካከል የቀጠለ ትብብር እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።

8ኛው ዙር ድርድር እ.ኤ.አ ከኖቬምበር 9-10 ቀን 2026 ዓ.ም ለሁለት ቀናት በጄኔቫ እየተካሄደ ይገኛል።

#አዲስሚዲያኔትዎርክ #የትዉልድድምጽ #አዲስአበባ #ኢትዮጵያ ትክክለኛውን የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ የትስስር አውታሮችን በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑን!

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review