የኢሬቻ ሆራ አርሰዲ በዓል የኢትዮጵያዊነትና የአብሮነት ድምቀት ነው

You are currently viewing የኢሬቻ ሆራ አርሰዲ በዓል የኢትዮጵያዊነትና የአብሮነት ድምቀት ነው

AMN – መስከረም 24/2019 ዓ.ም

የሰላም፣ የፍቅርና የአንድነት መገለጫ የሆነው የኢሬቻ ሆራ አርሰዲ በዓል በቢሾፍቱ ከተማ በድምቀትና በሰፊ ሕዝባዊ ተሳትፎ በድምቀት ተከብሯል።

የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል የኦሮሞ ህዝብ ብቻ የሚያከብረው ሳይሆን፣ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አብሮነትና ኢትዮጵያዊነት የሚንጸባረቅበት ታላቅ መድረክ ሆኗል።

በዓሉን ለማክበር ከተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎችና ከሀገር ውጪ የመጡ እንግዶችና ብሔር ብሔረሰቦች የተገኙ ሲሆን፤ ትላንት በአዲስ አበባ ሆራ ፊንፊኔ የተጀመረው የኢሬቻ በዓል ዛሬ በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ ተከብሯል።

ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኮንሶ አካባቢ የመጡ የባህላዊ ልኡካን ቡድንም በበዓሉ ላይ በመሳተፍ ልዩ ድምቀት ሰጥተውታል።

በበዓሉ ላይ የተሳተፉት የኮንሶ ብሔረሰብ ተወካይ አቶ ደርጉ ዱባ፤ በዓሉን ለመታደም በመቻላቸው የተሰማቸውን ታላቅ ደስታ ገልጸዋል።

ትላንት አዲስ አበባ ላይ በተከበረው በዓል ላይ እንደተሳተፍነው ሁሉ፣ ዛሬም እዚህ ቢሾፍቱ መገኘት እና ከተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በጋራና በአብሮነት ስሜት ማክበር መቻላችን ትልቅ ደስታ ፈጥሮብናል ብለዋል አቶ ደርጉዶ።

በዚህ በዓል መሳተፋቸው የመጀመሪያቸው መሆኑን የገለጹት አቶ ደርጉ ዱባ፤ ከግል ደስታቸው ባለፈ ለወከሉት ህዝብ ጭምር ትልቅ ኩራት እንደሆነ ተናግረዋል።

የኢሬቻ በዓል ፍቅር፣ ሰላም እና አንድነት የሚሰበክበት ልዩ መድረክ መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።

በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች በአንድ ላይ ሆነው በዓሉን ማክበራቸው ኢትዮጵያዊነትን፣ አብሮነትን እና ሰላምን በሚገባ ያሳየና ህዝቦችን ከማስተሳሰር አንጻር እጅግ ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

የኮንሶ ባህላዊ ልኡካን ቡድንም ሕዝባዊ ትስስርን በሚያጠናክር መልኩ በዓሉን ከኦሮሞ ህዝብ እና ከመላው ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በጋራ እያከበርን እንገኛለን ብለዋል፡፡።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review