AMN – ጥቅምት 10/2019 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሉዓላዊነና አንድነት ተከብሮ የኖረበት ምስጢር ሲነሳ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከአድዋ ጀግኖች አባቶቹ የወረሰው ጀግንነት እና ሀገር ወዳድነት መሆኑን ታሪክ ያስረዳል።
የዛሬው የሀገር መከላከያ ሠራዊትም ያንን ጀግንነት በመውረስ ብሎም እራሱን ዘመኑ በሚፈቅደው የወታደራዊ ሳይንስ እና የጦር መሳሪያዎች በማደራጀት ጦርነትን አስቀድሞ የሚጨርስ ስልት የተላበሰ መሆኑ ይነገርለታል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት የጀግንነት ምስጢር ከመደበኛ ወታደራዊ ስልጠናና ትጥቅ በዘለለ ከህዝብ የወጣ፣ የህዝብን ችግር የሚረዳና ለሀገር ሉዓላዊነት ቅድሚያ የሚሰጥ ህዝባዊነት ያለው በመሆኑ በየትኛውም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ የህዝብን እና የሀገርን ጥሪ በመቀበል ግዴታውን የሚወጣ በመሆኑ ነው፡፡
በዘመናዊው ዓለም የቴክኖሎጂና የደህንነት ውጥረት ውስጥ ታሪካዊ ጀግንነት ብቻውን በቂ አለመሆኑን የተገነዘበው የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የመዋቅር ማሻሻያ በማድረጉ በተቋሙ የተሰራው የሪፎርም ስራ ውጤት እያስገኘ መሆኑንም መረጃዎች ያስረዳሉ።
ሠራዊቱ አሁን ላይ የዘመነ አሰራር፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂ እና በመረጃ መረብ ደህንነት የዳበረ አቅም በመገንባቱ፣ የሀገሪቱን የአየር፣ የየብስና የቴክኖሎጂ ምህዳር በንቃት በመጠበቅ አንድም የጠላት ትንኮሳ እንዳይሳካ እያደረገው ይገኛል።

ይህ የቴክኖሎጂ ጥንካሬ ሀገራዊ ስጋቶችን ቀድሞ የመለየት፣ የመረዳት ብሎም የማክሸፍ አቅሙን በከፍተኛ ደረጃ አሳድጎታል።
በተለይም በመስክ ውጊያና የክትትል ስራዎች ላይ ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉ ዘመናዊ አየር ላይ የሚበሩ የክትትል መሣሪያዎች፣ የሳተላይት መረጃ ልውውጥ ሥርዓቶችና የራዳር ቴክኖሎጂዎች የሠራዊቱን የመምታትና የመከላከል አቅም ወደ ላቀ ደረጃ አሸጋግረውታል።
ከዚህ በተጨማሪም፣ የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት የጦር መሳሪያዎችን በራስ አቅም በመጠገን፣ በማሻሻልና ሌሎች ዘመናዊ መሳሪያዎችንም የማምረት አቅሙን በራሱ መሀንዲሶችና የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች በመገንባት ረገድ አስደናቂ ስኬት አስመዝግቧል።
የቴክኖሎጂው አቅም ግንባታ ከዘመናዊ ወታደራዊ ሳይንስና የሰለጠነ የሰው ሃይል ጋር በመቀናጀቱ፣ የሠራዊቱ አባላት የቴክኖሎጂ መሣሪያዎችን በላቀ ስነ-ምግባርና ሙያዊ ብቃት የመጠቀም ችሎታቸውን አሳድገዋል።
ይህ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የታጠቀ እንዲሁም በስነ ምግባር የታነጸ ሠራዊት የሀገርን ሉዓላዊነት፣ ሰላምና ደህንነት ከማስከበር ባለፈ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ ሰላምና ጸጥታን ለማረጋገጥ በሚደረጉ አህጉራዊ ግዴታዎች ላይ ውጤታማ አጋር እንዲሆን አስችሎታል።
በወርቅነህ አቢዮ