ለ”ሲቲ ማውንቴን ባይክ” (City Mountain Bike) ውድድር፦ የኢትዮጵያውያን ተወዳዳሪዎች ዝግጅት ምን ይመስላል?

You are currently viewing ለ”ሲቲ ማውንቴን ባይክ” (City Mountain Bike) ውድድር፦ የኢትዮጵያውያን ተወዳዳሪዎች ዝግጅት ምን ይመስላል?

AMN — ሚያዝያ 23/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ የሚካሄደው የ”ሲቲ ማውንቴን ባይክ” ዓለም አቀፍ የብስክሌት ውድድር ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለጸ። የትውልድ ድምፅም የሆነው AMN ከነገ በስተያ እሁድ የሚካሄደውን ይህንን ውድድር በቀጥታ ለማስተላለፍ ዝግጅቱን አጠናቋል። በተጨማሪም ውድድሩ ከ60 በላይ በሚሆኑ ሃገራት ሚዲያዎች የቀጥታ ስርጭት ሽፋን ያገኛል።

ኤኤምኤን ዲጂታል ይህንኑ አስመልክቶ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ክለብ አባላት የሚደረገውን ዝግጅት በስፍራው ተገኝቶ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ክለብ የብስክሌት ስፖርተኛ ሙዳሲር አስራት ፤ ኢትዮጵያና አዲስ አበባ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚያስተናግዱት በዚህ ዓለም አቀፍ ውድድር ላይ በብቃት ለመሳተፍና ለማሸነፍ ተስፋ እንዳለው ገልጾ፣ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ተናግሯል።

ሌላኛዋ ተወዳዳሪ ሌሎ ሁንዴ በበኩሏ፤ ይህ የመጀመሪያው የብስክሌት ውድድር ከፍተኛ ትኩረት እና ትግል የሚጠይቅ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያን በውድድሩ ለማስተዋወቅ የምትችለውን ሁሉ እንደምታደርግ ገልጻለች። በተጨማሪም ሰፊ ልምድ ካላቸው የሌላ አገር ስፖርተኞች ተሞክሮ ለመቅሰም ትልቅ ዕድል መሆኑን ጠቁማለች።

የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ክለብ አሰልጣኝ አልጋነሽ ገብረህይወት እንደገለጹት፤ የኮሪደር ልማቱና ለብስክሌት ውድድር የተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎች ታዳጊዎች ወደ ክለቡ መጥተው እንዲሰለጥኑ ማድረጉን ገልጸዋል። ለአዲስ አበባ አዲስ በሆነው በዚህ ውድድር ላይ ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ በቂ ዝግጅት መደረጉንም አክለዋል።

ሴት ስፖርተኞችም የሚሳተፉበት ይህ የ”ሲቲ ማውንቴን ባይክ” ውድድር፣ ዘርፉን በኢትዮጵያ ስም ወክለው የሚወዳደሩ ስፖርተኞችን ለማፍራት እንደ መልካም አጋጣሚ እንደሚጠቀሙበት ገልፀዋል።

ውድድሩ የኢትዮጵያን መልካም ስም ለዓለም ለማስተዋወቅና አዲስ አበባ ለዓለም አቀፍ ኩነቶች ያፈራቻቸውን የልማት ውጤቶች ለማሳየት እንደሚረዳ ተጠቁሟል። ስፖርተኞቹም የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ ይህንን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንደሚወዳደሩ ገልጸዋል።

በመልካሙ አበበ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review